በዴሞክራቲክ ኮንጎ በተባባሰው ግጭት በርካታ ቁጥር ያላቸው እስረኞች ከእስር ቤቶች ማምለጣቸው ተነገረ
ከጥር ወር ጀምሮ ከአንድ እስር ቤት ከ4 ሺህ በላይ እስረኞች አምልጠዋል

እስረኞች ባመለጡባቸው አካባቢዎች በተለያዩ ወንጀሎች እና የበቀል እርምጃዎች ላይ በስፋት መሳተፋቸው የሰብዓዊ ቀውሱን አባብሶታል
በሩዋንዳ የሚደገፉት የኤም 23 አማፂያን ባለፉት ሁለት ወራት በምስራቃዊ የሀገሪቱ ከፍል ሁለት ትላልቅ ከተሞች መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የጅምላ እስር ቤት ማምለጥ መበራከት በህዝቡ ላይ ሽብር ፈጥሯል።
አማጺያኑ በከተሞች የሚያርጉት እንቅስቃሴ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ ከጥር ወር ጀምሮ ከአራት እስርቤቶች በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች አምልጠዋል፡፡
የማረሚያ ቤቶች ጠባቂያዎች ታሳሪዎች እንዳያመልጡ ለቀናት ጥበቃ ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆኑም በአማጺያኑ በተከፈተባቸው ተኩስ እስርቤቶቹን ጥለው እንደሸሹ ነው የተነገረው፡፡
በጥር 27 ምሽት የኤም 23 ታጣቂዎች የሰሜን ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ጎማ ከተማ ሲገባ ከ4 ሺህ በላይ እስረኞች ከጎማ ሙንዜንዜ እስር ቤት አምልጠዋል።
ቀጥሎም ታሳሪዎቹ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሴት እስረኞች ላይ የአስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶችን መፈጸማቸው ተዘግቧል፡፡
የእንግሊዙ ዘ ጋርዲን ጋዜጣ ይዞት በወጣው ዘገባ ከጎማ እስር ቤት ባለፈ በቡካቩ ፣ ካባሬ እና ካሌማ ማዕከላዊ እስርቤት ጨምሮ ከበርካታ ስፍራዎች አደገኛ የሚባሉ ወንጀለኞች አምልጠዋል፡፡
እስረኞቹ በአስገድዶ መድፈር፣ በግድያ፣ በአመጽ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ፣ ገንዘብ በማጭበርበር እና የህዝባዊ ጸጥታ በማደፍረስ ወንጀሎች ተፈርዶባቸዋል።
በስፍራው የሚንቀሳቀሱ የጸጥታ እና የደህንነት ተንታኞች ታሳሪዎቹ ለእስር ባበቋቸው ግለሰቦች ፣ ከሳሾች እንዲሁም የፍትህ እና የጸጥታ አካላት ላይ የቂም በቀል እርምጃ እየወሰዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በጎማ እና ቡካቩ ከተሞች ያመለጡ እስረኞች የቆሸሹ ጠመንጃዎችን እና ሌሎች የስለት የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ ዝርፊያን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎች ላይ ተሰማርተው መመልከታቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ ምስራቃዊ ኮንጎ ከተሞች የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ከተማዎቹ ከተያዙ በኋላ ሥራ አቁመዋል።
በጎማ እና ቡካቩ በመንግስት ምትክ የሚንቀሳቀሰው ኤም23ን ጨምሮ የሚሊሻዎች ጥምረት የሆነው “አሊያንስ ፍሌቭ ኮንጎ” እስር ቤቶችን ለመገንባት እና ለማደስ ቃል ገብቷል።
ነገር ግን በስፍራው የሚፈጸሙ ወንጀሎች መበራከት በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች ደህንነት ከፍተኛ ስጋት ሆኖ መቀጠሉ ተዘግቧል፡፡