በኩርስክ ግዛት የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬንን ኃይሎችን ወደ ኋላ በመክበብ ወደ ፊት እየገሰገሱ ነው
የሩሲያ ኃይሎች ወደፊት መግፋት የከበባ ስጋት የፈጠረው ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር በሳኡዲ አረቢያ ለመነጋገር እየተዘጋጀች ባለበት ወቅት ነው

የዩክሬን ወታደሮች ባለፈው ነሀሴ ወር በምዕራብ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት 1300 ስኩየር ኪሎሜትር ስፋት ያለው ቦታ ተቆጣጥረው ነበር
በኩርስክ ግዛት የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬንን ኃይሎችን ወደ ኋላ በመክበብ ወደ ፊት እየገሰገሱ ነው።
በኩርስክ ግዛት የሩሲያ ኃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የዩክሬን ኃይሎች እንዲያፈገፍጉ ወይም እጅ እንዲሰጡ ለማድረግ በማለም በከፈቱት ትልቅ የከበባ ዘመቻ የዩክሬን ኃይሎችን ወደ ኋላ በመክበብ ወደ ፊት እየገፉ እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ ኃይሎች ወደፊት መግፋት የከበባ ስጋት የፈጠረው ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር በሳኡዲ አረቢያ ለመነጋገር እየተዘጋጀችና የአሜሪካ ፕሬዝደንት ትራምፕ ጦርነቱ በፍጥነት እንዲቆም ጫና እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው።
የዩክሬን ወታደሮች ባለፈው ነሀሴ ወር በምስራቅ ዩክሬን ያለውን የሩሲያን ኃይል ለማዛባትና ወደፊት ከሩሲያ ጋር በሚደረግ ንግግር እንደመደራደሪያ ለመጠቀም በምዕራብ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት 1300 ስኩየር ኪሎሜትር ስፋት ያለው ቦታ ተቆጣጥረው ነበር።
ነገርግን ሩሲያ በየካቲት ወር አጋማሽ 800 ስኩየር ኪሎሜትር የሚሆነውን መልሳ መቆጣጠር የቻለች ሲሆን በቅርብ ቀናት ከበርካታ አቅጣጨዎች በፈጸመችው መልሶ ማጥቃት ደግሞ የዩክሬን የአቅርቦት መስመር እና መውጫ መስመር ለመዝጋት እየተቃረበች ነው።
ሮይተርስ የሩሲያን የጦር ጸኃፊ ቱ ሜጀርስን ጠቅሶ እንደዘገበው የሩሲያ ኃይሎች የኢቫሾቭስኪን መንደር ማጽዳታቸውንና በኩርስክ ግዛት "ኳልድሮን" ወደተባለችው ቦታ ቢያንስ በሰባት አቅጣጫ እየቀረቡ ናቸው። ሌላኛው ታዋቂ የጦር ጸኃፊ ዩሪ ፖዶሊያካ የሩሲያ ግስጋሴ ፈጣን በመሆኑ ምክንያት ሁሉንም መረጃዎች ለመግኘት መቸገሩን ገልጿል።
ለሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ቅርብ የሆነው የጦር ጸኃፊ ራይባር ደግሞ "የሩሲያ ኃይሎች ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ባለፉት ሁለት ወራት ከፈጸሙት በተሻለ መልኩ በኩርስክ ግዛት ቦታ እየተቆጣጠሩ ነው"ብሏል።
ዋናው ግንባር መሰበሩን የገለጸው ራይባር የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬን ኃይሎች ከኩርስክ ወደ ዩክሬኗ ሱሚይ ግዛት እንዳይወጡ ለማድረግ ምሽግ መያዛቸውን ጠቅሷል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ሶስት አመት ያስቆጠረውን ጦርነት ለማስቆም ከፕሬዝዳንት ፑቲንና ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ጋር እየተነጋገሩ ይገኛሉ።