ከረዳት ሰራተኛቸው ጋር ሲሳሳሙ የታዩት የብሪታኒያ የጤና ሚኒስትር ከኃላፊነት ለቀቁ
ጠ/ሚ ቦሪስ ጆንሰንም በተሰናባቹ ሚኒስትር ቦታ አዲስ ሚኒስትር ሰይመዋል
ሚኒስትሩ የኮሮናን ሕግ በመጣሳቸውም ይቅርታ ጠይቀዋል
የብሪታኒያ የጤና እና ማህበራዊ ዋስትና ሚኒስትር ማት ሃንኩክ ከረዳታቸው ጋር ሲሳሳሙ በሲሲቲቪ ካሜራ ከታዩ በኋላ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄውን ያቀረቡት ከረዳታቸው ጋር መሳሳማቸውን ተከትሎ አካላዊ ርቀት እንዲጠበቅ የሚያዘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የቁጥጥር ህግ በመጣሳቸው ነው፡፡
ይህንንም በይፋዊ የግል የትዊተር ማህበረሰብ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ሃንኩክ በጽሁፋቸው “የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን ሕግ ያዘጋጀን አካላት ለሕጉ ተገዥ መሆን ነበረብን” በማለት ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ እና እርሳቸው ቢሮ ውስጥ የምትሰራ ረዳታቸው ሲሳሳሙ የሚያሳይ ቪዲዮ ከሰሞኑ በሲሲቲቪ ካሜራ ተቀርጾ ተለቋል፡፡
ቪዲዮውን ለዓለም ያሰራጨው ዘ ሰን የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ ነው፡፡
ጋዜጣው ይህንን ቪዲዮ በገጹ ካሰራጨ በኋላ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ማት ሃንኮክም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን ርቀትን መጠበቅ የሚለውን መመሪያ መጣሳቸውና ቤተሰባቸውን መበደላቸውን በሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸው ላይ ጽፈዋል፡፡
ከሚኒስትሩ ጋር ስትሳሳም የተያዘችው የእርሳቸው ረዳት ጂና ኮላድንግሎን ልክ እንደ ማት ሃንኩክ ሁሉ ባለትዳር መሆኗን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሚኒስትሩ ላለፉት ሶስት ዓመታት የሀገሪቱ ጤና ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ለጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ባቀረቡት የሥራ መልቀቂያ መሰረት ከኃላፊነት ለቀዋል፡፡
ማት ሃንኩክ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ባቀረቡት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ላይም ሀገራቸውን ከጀርባ ሆነው ማገልገላቸውን እንደሚቀጥሉና በማንኛውም አጋጣሚ የብሪታኒያ ሕዝብን ማገልገል እንደሚፈልጉ ቀጣይ ጊዜያትን ከልጆቻቸው ጋር እንደሚያሳልፉ በመጠቆም፡፡
ማት ሃንኮክን በመተካት፤ ሳጅድ ጃቪድ የብሪታኒያ የጤና እና ማህበራዊ ዋስትና ሚኒስትር እንዲሆኑ መመረጣቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
አዲሱ የካቢኔ አባልም ለዚህ ኃላፊነት በመመረጣቸው ደስተኛ መሆናቸውን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡