የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬድየቭ “ሩሲያ በዩክሬን ያላትን አላማ ታሳካለች” አሉ
ሜድቬድየቭ “ምዕራባውያን ሩሲያን ለማጥፋት የረዥም ጊዜ እቅድ አላቸው” ሲሉም አስጠነቅቀዋል
ሜድቬድየቭ “ምዕራባውያን ሩሲያን ለማጥፋት የረዥም ጊዜ እቅድ አላቸው” ሲሉም አስጠነቅቀዋል
የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬድየቭ “ሩሲያ በዩክሬን ያላትን አላማ ታሳካለች” አሉ፡፡
የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ሰው እንደሆኑ የሚነገርላቸው ዲሚትሪ ሜድቬድየቭ ፤ “ምዕራባውያን ሩሲያን ለማጥፋት የረዥም ጊዜ እቅድ አላቸው” ሲሉም ከሩሲያው ኒውስ ኤጀንሲ ታሳ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሩሲያ የጸጥታ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ፤ "ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደች ነው እናም በምትፈልገው መልኩ ሰላምን እያመጣች ነው" ማለታቸውም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሜድቬድየቭ፤ እንደፈረንጆቹ የ2008 የጆርጂያ ጦርነት ፣ የኔቶ ወታደራዊ ህብረት ማጠናከር እና የአሁኑ የዩክሬን ጦርነት፤ አሜሪካ ና አጋሮቿ ሩሲያን ለማጥፋት እስካሁን ያደረጓቻ ሙከራዎች አካል መሆናቸውም በአብነት አንስተዋል።
"ዓላማው አንድ ነው፤ ሩሲያን ለማጥፋት" ሲሉም አክለዋል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬድየቭ፡፡
በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በእቅዳቸው መሰረት እየሄደ መሆኑን ፕሬዝዳንት ፑቲን ቀደም ሲል ገልጸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
"በዩክሬን ያለው ጦራችን በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተልዕኮውን በሚገባ እየፈጸመ ነው፣ በዩክሬን መስራት ያለብንን ስራዎች ሁሉ እያከናወኑ ነው"ም ነበር ያሉት ፕሬዘዳንት ፑቲን፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ከወራት በፊት በሰጡት አጭር መግለጫ “ሊስቆመን የሚሞክር፣ በሀገራችን እና በህዝባችን ላይ ተጨማሪ አደጋ የሚጥል ማንኛውም አካል በታሪኩ አይቶት የማያውቀው እጣፋንታ ይገጥመዋል” ሲሉ ምእራባውያን ማስጠንቀቃቸውም አይዘነጋም፡፡
የሩሲያ ምላሽ ፈጣን እንደሚሆን የገለጹት ፕሬዝዳንት ፑቲን የወታደራዊ ዘመቻው አላማ በኪቭ አስተዳደር ለበርካታ አመታት ጥቃት እና የዘርማጥፋት ሲፈጸምባቸው የነበሩትን ዜጎች መታደግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡