ሩሲያ ከኔቶ ለዩክሬን የተለገሱ 45 ሺህ ቶን ጥይት አወደምኩ አለች
ጥይቱ የወደመው በደቡባዊ ዩክሬን ግዛት ባለ አንድ የጦር መሳሪያ መጋዝን እንደሆነ ተገልጿል
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ዛሬ 166ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
ሩሲያ ከኔቶ ለዩክሬን የተለገሱ 45 ሺህ ቶን ጥይት ማውደሟን ገለጸች።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር እንደገለጸው ሩሲያ ለዩክሬን ከኔቶ አባል ሀገራት የተውጣጣ 45 ሺህ ቶን ጥይት ማውደሟን አስታውቃለች።
በደቡባዊ ዩክሬን ግዛት እንደሚገኝ የተገለጸው ይህ የዩክሬን የጦር መሳሪያ መጋዘን ሩሲያ በአየር ላይ በተሰነዘረ ጥቃት መጋዝኑን እንዳወደመች አርቲ ዘግቧል።
የሩሲያ ጦር ከዚህ የጦር መጋዝን ባለፈ አምስት ተጨማሪ የዩክሬን የጦር መሳሪያ መጋዝኖችን እንዳወደመም አስታውቋል።
በሩሲያ ጦር እንደወደሙ የተገለጹት እንዚህ የጦር መሳሪያ መጋዝኖች በቅርቡ ከአሜሪካ እና ምዕራባውያን ሀገራት የተለገሱ የጦር መሳሪያዎች ተከማችተውባቸው እንደነበር ዘገባው አክሏል።
ይሁንና እነዚህ የዩክሬን የጦር መሳሪያ መጋዝኖች በሩሲያ ጦር ጥቃት ስለመውደማቸው ከዩክሬን በኩል እስካሁን የተሰጠ መረጃ ወይም መግለጫ የለም።
አሜሪካ አንድ ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለዩክሬን ልታስታጥቅ መሆኑን በትናንትናው ዕለት ማስታወቋ ይታወሳል።
በአጠቃላይ ሩሲያ እና ዩክሬን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አሜሪካ ለዩክሬን የለገሰቻቸው የጦር መሳሪያ 8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ እንዳላቸው ተገልጿል።
በአሁኑ የጦር መሳሪያ ልገሳ ፓኬጅ መሰረት ለዩክሬን ከሚሰጡ የጦር መሳሪያዎች መካከል ሂማርስ፣ ናስማስ፣ ኤም113 እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
እነዚህ የጦር መሳሪያዎች ዩክሬን ከሩሲያ ለሚሰነዘሩባት የየብስ፣ባህር እና አየር ላይ ጥቃቶችን ለመመከት ያስችላታል ተብሏል።
ይህ አዲሱ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዛሬ እንደሚፈረም የሚጠበቅ ሲሆን በጥንቃቄ ወደ ዩክሬን ይጓጓዛል ተብሏል ።
ሩሲያ በበኩሏ ምዕራባውያን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ማስታጠቃቸውን እንዲያቆሙ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ባለፉት ጊዜያት ውስጥም አሜሪካንን ጨምሮ ከምዕራባዊያን ለዩክሬን የተለገሱ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን አውድሜያለሁ ማለቷም አይዘነጋም።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በየዕለቱ እስከ 200 ወታደሮች በሩሲያ ጥቃት እየተገደሉባቸው እንደሆነ ገልጸው ምዕራባውያን የጦር መሳሪያ እንዲለግሱም ጥሪ አስተላልፈው ነበር።