በ18 አመቱ ከንቲባ ሆኖ የተመረጠው አሜሪካዊ አዲስ ታሪክ አፅፏል
የኮሌጅ ተማሪው ጀይለን ሰሚዝ በአርካንሳስ ግዛት የምትገኝ ከተማን ለመምራት የተደረገውን ምርጫ አሸንፏል
ስሚዝ "የኔ ድል ወጣቶች ወደ መሪነት እንዲመጡ ያነቃቃል" ብሏል
አሜሪካ በእድሜ ትንሹን ከንቲባ በአርካንሳስ ግዛት አግኝታለች።
የ18 አመቱ ጀይለን ሰሚዝ በግዛቷ ኧርል የተባለች ከተማን በከንቲባነት እንዲመራ ተመርጧል።
ሰሚዝ ተፎካካሪውን ኔሚ ማቲውስ አሸንፎ ከንቲባ እንዲሆን የከተማዋ ነዋሪዎች በድምፃቸው ይሁንታን ሰጥተውታል ነው የተባለው።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ባለፈው አመት አጠናቆ በዚህ አመት ኮሌጅ የገባው ሰሚዝ፥ ከሚሲሲፒ ወንዝ በቅርብ ርቀት የምትገኘውን የኧርል ከተማ እንዲመራ በመመረጡ ደስታውን ገልጿል።
"እናቴ ማሸነፌን እስካሁን አላመነችም" ያለው ወጣቱ ከንቲባ፥ በማህበራዊ ትስስር ገፁ አምነውበት ድምፅ የሰጡትን ነዋሪዎች አመስግኗል።
"የኔ ድል ብዙዎችን ያነቃቃል ብዬ አስባለሁ፤ በተለይ ወጣቶች ወደ መሪነት መጥተው የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት እንዲያስቡ ከወዲሁ ዝግጁ እንዲሆኑም ያግዛል" ነው ያለው ስሚዝ።
በኧርል ከተማ የለውጥና የመሪነት ተምሳሌት ለመሆን እንደሚሰራም ቃል ገብቷል።
ስሚዝ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገባቸውን የህብረተሰብ ጤናን ማሻሻል፣ የትራንስፖርትና የምግብ መደብሮች አቅርቦትን የማሻሻል ስራዎች ትኩረት አደርግባቸዋለው ብሏል።
2 ሺህ ሰዎች በሚኖሩባት ከተማ የተዘጉ ቤቶችን የማደስ ተግባርንም ቅድሚያ እንደሚሰጠው ነው ያስታወቀው።
የአሜሪካ በእድሜ ትንሹ ጥቁር ከንቲባው ጀይለን ስሚዝ ከኮሌጅ ትምህርቱ ጎን ለጎን የአርካንሳሷን ኧርል ከተማ በከንቲባነት ይመራል።