ፑቲን ኦሬሽኒክ የተባለውን ሚሳይል ወደ ጎረቤት ቤላሩስ ሊልኩ እንደሚችሉ ተናገሩ
ፑቲን ቤላሩስ በግዛቷ ውስጥ የሚሰማሩትን ኦሬሽኒክ ሚሳይሎች ኢላማ ትወስናለች ብለዋል

ሩሲያ ባለፈው ወር በኦሬሽኒክ ሚሳይል የዩክሬንን ከተማ መትታለች
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ 'ኦሬሽኒክ' የተባለውን የመካከለኛ ርቀት ባለስቲክ ሚሳይል በ2025 መጨረሻ ወደ ቤላሩስ ልትልክ ትችላለች ሲሉ ተናግረዋል።
ፑቲን ይህን ያሉት በቤላሩሱ ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሸንኮ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ነው። ፑቲን ቤላሩስ በግዛቷ ውስጥ የሚሰማሩትን ኦሬሽኒክ ሚሳይሎች ኢላማ ትወስናለች ብለዋል።
ሩሲያ ባለፈው ወር በኦሬሽኒክ ሚሳይል የዩክሬንን ከተማ መትታለች።
ሩሲያ እጅግ ፈጣን የተባለውን ይህን ሚሳይል ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከየካቲት 2022 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመችው ምዕራባውያን ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይል ተጠቅማ ሩሲያ ግዛት ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ መፍቀዳቸው ተከትሎ ነበር።
ሩሲያ አዲስ ሚሳይል ያስወነጨፈችው በጦርነቱ ዙሪያ ምዕራባውያን የሚያሳልፏቸው ሌሎች ውሳኔወችን ዝም ብለ እንዳማታልፍ ለማስጠንቀቅ ጭምር እንደነበር ተገልጿል። ፕሬዝደንት ፑቲን ሩሲያ በጦርነቱ አዲስ ሚሳይሎችን መጠቀሟን እንደምቀጥልበት መግለጻቸው ይታወሳል።
ዩክሬን በዚህ ሚሳይል የደረሰባትን የጉዳት መጠን ግልጽ ባታደርግም፣ ሚሳይሉ እጅግ ፈጣን እና አሁን ባላት የአየር መከላከያ ስርአት ማክሸፍ አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጻለች።
ሩሲያ እንደገለጸችው ሚሳይሉ የአሜሪካን ምዕራባዊ ክፍል እና አውሮፓው ውስጥ ያሉ የትኞቹንም ኢላማዎችን የመምታት አቅም አለው።
ሩሲያ እና ዩክሬን ያቀረባቸው የንግግር ቅድመ ሁኔታዎች የተራራቁ በመሆናቸው ምክንያት ጦርነቱን ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም።
ሩሲያ ጦርነቱ እንዳቆም በከፊል የያዘቻቸውን አራት ግዛቶች ይዞ መቀጠል እንዳለበት ስትገልጽ ፣ ዩክሬን ደግሞ የሩሲያ ጦር ሙሉ በሙሉ መውጣትን በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጣለች።