ሜሲ በ13 አመቱ ለባርሴሎና የፈረመባት ናፕኪን (ሶፍት) ለጨረታ ቀረበች
የክለቡ የወቅቱ ዳይሬክተር ካርለስ ሬክሳክ የፈረሙባት ታሪካዊ ሰነድ በ300 ሺህ ፓውንድ መነሻ ዋጋ ነው ለጨረታ የቀረበችው
አርጀንቲናዊው ኮከብ ለካታላኑ ክለብ 778 ጊዜ ተሰልፎ 672 ጎሎችን አስቆጥሯል
ሊዮኔል ሜሲ በ13 አመቱ የስፔኑ ታላቅ ክለብ ባርሴሎናን መቀላቀሉ በፊርማ የተረጋገጠባት ናፕኪን (ሶፍት) ለጨረታ ልትቀርብ ነው።
ናፕኪን (ሶፍቷ) በፈረንጆቹ 2000 የወቅቱ የባርሴሎና ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ካርለስ ሬክሳክ ሜሲ ክለባችን እንዲቀላቀል ፈቅጃለሁ ብለው የፈረሙባት የመጀመሪያ የዝውውር ውል ናት።
ሜሲ በካታላኑ ክለብ ቀደም ብሎ ባደረጋቸው ሙከራዎች ምላሽ ያለማግኘቱ ስጋት የገባቸው አባቱ ሆርጌ ከባርሴሎና ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ካርለስ ሬክስክ ጋር ምሳ በልተው በጉዳዩ ከተነጋገሩ በኋላ ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ከመያዝ ይልቅ በቅርብ ባገኙት እጅ መጠራረጊያ ናፕኪን (ሶፍት) ውል ማሰርን መርጠዋል።
የስፔኑ ክለብ የተጫዋቾች ዝውውር አማካሪው ጆሴፍ ሚንጉየል እና የአርጀንቲናዊው የወቅቱ ታዳጊ ተጫዋች መልማይና ወኪል ሆራሲዮ ጂዮሊም ፊርማቸውን አኑረዋል።
ሰማያዊ ቀለም ባለው ብዕር ናፕኪን ወይም ሶፍት ላይ የተጻፈው ውልም፥ “ባርሴሎና በታህሳስ 14 2000 ሊዮኔል ሜሲን ለማስፈረም ወስኗል፤ ይህንንም የክለቡ ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ካርለስ ሬክሳክ፣ የተጫዋቾች ዝውውር አማካሪው ሆራሲ ጂዮሎም ተጫዋቹን ለማስፈረም መወሰናቸውን በፊርማቸው አረጋግጠዋል” ይላል።
በናፕኪን በሰፈረ ውል ባርሴሎናን የተቀላቀለው ሜሲ የክለቡን የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ መሆን ችሏል።
ከ16 አመቱ ጀምሮ ለካታላኑ ክለብ 778 ጊዜ ተሰልፎ 672 ጎሎችን ማስቆጠሩም የሚታወስ ነው።
በ2021 ወደ ፈረንሳዩ ፒኤስጂ እስኪያመራ ድረስም 10 የላሊጋና አራት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ስኬቶችን ከልጅነት ክለቡ ጋር ተቀዳጅቷል።
አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ፈርጥ ከባርሴሎና ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ውል ያሰረባት ናፕኪን (ሶፍት) በብሪታንያው የጨረታ ኩባንያ ቦንሃምስ በኩል በመጋቢት ወር ለጨረታ ትቀርባለች።
ምግብ በልተን እጅና አፋችን የምንጠራርግባት ናፕኪን የሜሲን ህይወት ቀይራለች፤ የባርሴሎናን የድል ጉዞ ዘውራለች፤ በመላው አለም በቢሊየን ለሚቆጠሩ እግርኳስ አፍቃሪዎችም የኳስ ጥበበኛውን አስተዋውቃለችና የጨረታ የመነሻ ዋጋዋ 300 ሺህ ፓውንድ ይሆናል ተብሏል።