ሜሲ ወደ ሳኡዲ ያደረገው ጉዞ ከፈረንሳዩ ክለብ ጋር ር ለመለያየት መቃረቡን ያሳያል ተብሏል
ፓሪስ ሴንት ጀርሜን ሊዮኔል ሜሲን ለሁለት ሳምንት ማገዱ ተነግሯል።
አርጀንቲናዊው ተጫዋች ክለቡን ሳያስፈቅድ ወደ ሳኡዲ አረቢያ በመጓዙ ነው እገዳው የተጣለበት ብሏል ሲኤንኤን በዘገባው።
ዘገባው ሜሲ ከትናንት በስቲያ ሰኞ በልምምድ ላይ እንዳልተገኘ ጠቁሟል።
በልምምድ ሳይገኝም ከፈረንሳይ ውጭ የማስታወቂያ ስራ ላይ ነበር ተብሏል።
የሰባት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ በሳኡዲ ከቤተሰቦቹ ጋር ሲዝናና የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
የሳኡዲ የቱሪዝም ሚኒስትር አህመድ አል ካቴብ “ሜሲና ቤተሰቦቹ አስደናቂ የሳኡዲ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመጎብኘት መጥተው ስለተቀበልኳቸው ደስተኛ ነኝ” የሚል ጽሁፍ የታከለበት መልዕክትና ምስሎችን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ሜሲ በራሱ የኢንስታግራም ገጹ ላይ ከአራት ቀናት በፊት የሳዑዲን የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚያስተዋውቅበትን ምስል ማጋራቱም የሚታወስ ነው።
“ሳዑዲ እንዲህ አረንጓዴ መሆኗን ማን ያስባል?፤ እስከቻልኩ ድረስ ብዙም ያልታወቁ ድንቅ ስፍራዎችን መጎብኜቴን እቀጥላለሁ፥ ሳኡዲን ጎብኙ” የሚል ማስታወቂያ ሰርቷል።
የሊዮኔል ሜሲ እና የፈረንሳዩ ክለብ ውል በሰኔ ወር መጨረሻ ይጠናቀቃል።
የ35 አመቱ ተጫዋች የሳኡዲ ጉብኝትም ከፒኤስጂ ጋር ለመለያየት መቃረቡን ያሳያል የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
የሳኡዲው ክለብ አልሂላል ሊዮኔል ሜሲን የአለም የተጫዋቾች ዝውውርን በመስበር ሜሲን ለማስፈረም ጥያቄ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።