ሊዮኔል ሜሲ በነጻ ዝውውር ወደ ባርሴሎና ሊመለስ ይችላል ተባለ
ሜሲ፤ ከክፍያ ጋር በተያያዘ ባርሴሎናን ለቆ የፈረንሳዩ ሻምፒዮን ፒ.ኤስ.ጂን የተቀላቀለው በ2021 ነበር
አርጀንቲናዊው ኮከብ 7 ጊዜ ባሎንዶርን በማሸነፍ ደማቅ የእግር ኳስ ታሪክ ማጻፍ ችሏል
የፓሪስ ሴንት ዠርሜይን የፊት መስመር ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ በነጻ ዝውውር ወደ ባርሴሎና ሊመለስ ይችላል እየተባለ ነው፡፡
የ35 አመቱ ሜሲ በእግር ኳስ ዘመኑ ለረጅም አመታት የተጫወተበት ክለብ ባርሴሎና መሆኑ ይታወቃል፡፡
ባርሴሎና ከሁለት አመታት በፊት ይፋ በተደረገው የላሊጋ የፋይናንሻል ህግ መሰረት ለሊዮኔል ሜሲ አዲስ ኮንትራት ማቅረብ ባለመቻሉ ተጫዋቹን ማቆየት እየፈለገም ቢሆን ለመልቀቅ መገደዱ አይዘነጋም፡፡
በመጨረሻም በ2021 ከክፍያ ጋር በተያያዘ ሜሲ ባርሴሎናን ለቆ የፈረንሳዩ ሻምፒዮን ፒ.ኤስ.ጂን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡
ሜሲ ከባርሴሎና ቢወጣም የክለቡ አመራሮች ተጫዋቹን በድጋሚ ወደ ካምፕ ኑ የማምጣት ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
የአሜሪካው ስፖርት ቻናል ኢኤስፒኤን አሁን ላይ ይዞት የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው ከፒ.ኤስ.ጂ ጋር ያለውን ኮንትራት ሊያጠናቀቅ ሶስት ወራት ብቻ የቀረው ሜሲ ወደ ባርሴሎና ሊመለስ ይችላል፡፡
እንዴት እና መቼ ለሚለው ግን በግልጽ የተባለ ነገር የለም ተብሏል፡፡
ሜሲ ወደ ባርሴሎና ሊመለስ ይችላል ቢባልም በፒ.ኤስ.ጂ በኩል ተጫዋቹን የማቆየት ፍላጎት እንዳለ ነው የሚነገረው፡፡
ተጫዋቹ በክለቡ የበላይ አመራሮች አዲስ ውል እንደቀረበለትም ጭምር መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ጠቢብ ሜሲ ወደ አሜሪካ በማቅናት በሜጀር ሊግ ሶከር ሊጫወት ይችላል የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጅ ባርሴሎናዎች የሜሲን ፍላጎቶች የሚያሟሉ ከሆነ ተጫዋቹን በድጋሚ የራሳቸው ማድረግ ይችላሉ እየተባለ ነው፡፡
በተጨማሪም የሜሲ የቀድሞ የቡድን አጋር የባርሴሎናው አሰልጣኝ ዣቪ ሄርናንዴዝ አርጀንቲናዊው ኮከብ ወደ ስፔን እንዲመለስ ሊያግባባው ይችላል የሚሉ መረጃዎችም እየወጡ ነው ፡፡
አርጀንቲናዊው ኮከብ 7 ጊዜ ባሎንዶርን በማሸነፍ በእግር ኳስ ደማቅ ታሪክ መጻፍ የቻለ ተጫዋች መሆኑ ይታወቃል፡፡
በቅርቡ ኳታር ባሰናዳቸው የ2022 የዓለም ዋንጫ ላይም ቢሆን የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድንን በመምራት ሀገሩ የውድድሩ አሸናፊ እንድትሆን ያደረገ ድንቅ ተጫዋች ነው፡፡
በዚህም የ2022 የፊፋ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ክብርን ሊቀዳጅ መቻሉ የሚታወስ ነው።