የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ የ91 ሚሊየን ዩሮ ቅጣት ተላለፈበት
ሜታ የተጠቃሚዎችን የይለፍ ቃል ደህንነት አልጠበቀም በሚል በአየርላንድ በቀረበበት ክስ ነው የተቀጣው
ሜታ በአውሮፓ ህብረት የመረጃ ጥበቃ ህግን በመተላለፍ እስካሁን የ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ቅጣት ተላልፎበታል
የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ 91 ሚሊየን ዩሮ (101.5 ሚሊየን ዶላር) ተቀጣ።
የአየርላንድ የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽን (ዲፒሲ) ሜታ የተጠቃሚዎችን የይለፍ ቃል ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ሳያደርግ “በግዴለሽነት” በውስጣዊ ስርዓቱ ውሰጥ አስቀምጧል ማለቱን ተከትሎ ከ2019 ጀምሮ ምርመራ ሲደረግበት ቆይቷል።
ሜታም የተወሰኑ ተጠቃሚዎቹን የይለፍ ቃል ሳይቀይር ማስቀመጡን አልካደም ነበር።
የተጠቃሚዎች የይለፍ ቃላት በሌላ ወገን ገብተው ለጥቃት እንዳያጋልጡ በኩባንያው ተቀይረው መቀመጥ እንዳለባቸው የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ግራሀም ዶይሌ ይናገራሉ።
ሜታ ግን የተጠቃሚዎችን የይለፍ ቃላት ሳይቀይርና በሚነበብ መልኩ በውስጣዊ የመረጃ ስርአቱ ውስጥ ማከማቸቱን ነው ያብራሩት።
ምክትል ኮሚሽነሩ በጥር ወር 2019 የተፈጸመ የመረጃ ብርበራ በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የሚገኙ የ36 ሚሊየን የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ተጠቃሚዎችን አደጋ ላይ መጣሉን አውስተዋል።
ኩባንያው ግን ጉዳዩን ለአየርላንድ የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽን አለማሳወቁን ተችተዋል ብሏል ፍራንስ24 በዘገባው።
የሜታ ቃልአቀባይ በበኩላቸው ኩባንያው በአየርላንድ የዳታ ፕሮሬክሽን ኮሚሽን (ዲፒሲ) ጥቆማው እንደቀረበ ወዲያውኑ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱንና የይለፍ ቃላቶቹ ተሰርቀው በጠላፊዎች እጅ ስለመውደቃቸው እስካሁን ምንም አይነት ማስረጃ እንደሌለ ተናግረዋል።
ሜታ በ2018 በይፋ የተዋወቀውን የአውሮፓ ህብረት የመረጃ ጥበቃ ህግ በመተላለፍ ተከሶ እስካሁን የ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዩሮ ቅጣት ተላልፎበታል።
ኩባንያው በ2023 የተላለፈበትን የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዩሮ ቅጣት ለማስነሳትም ይግባኝ መጠየቁ የሚታወስ ነው።
ጎግል፣ አፕል እና ሜታን ጨምሮ በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መቀመጫቸውን አየርላንድ ደብሊን ማድረጋቸውን ተከትሎ ኩባያዎቹ የአሰራር ግድፈት ሲኖራቸው ተጠያቂ የሚያደርጋቸው የአየርላንዱ ዲፒሲ ነው።
ደብሊን በያዝነው መስከረም ወርም በጎግል የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልማት ላይ ምርመራ መጀመሯ ይታወሳል።