ሜታ ታዳጊ ተጠቃሚዎቹን ለአደጋ እያጋለጠ ነው - አሜሪካ
የአሜሪካ የንግድ ኮሚሽን፥ ኩባንያው ከ13 እመት በታች የሆኑ ህጻናት እንዳሻቸው መልዕክት እንዲለዋወጡ መፍቀዱን አረጋግጫለሁ ብሏል
ሜታ በበኩሉ የሚነሳብኝ ቅሬታ ተገቢ አይደለም፤ “ፖለቲካዊ አላማ ያለው ነው” በሚል ተቃውሟል
የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ እናት ኩባንያው ሜታ የአሜሪካ የንግድ ኮሚሽን ወቀሳ ቀርቦበታል።
ሜታ ህጻናት እና ታዳጊዎች መተግበሪያዎችን ሲጠቀሙ ጥብቅ የቤተሰብ ክትትል እንዲደረግላቸው አላደረገም፤ የተቀመጡ መመሪያዎችንም አልፈጸመም የሚል ነው ክሱ።
በገለልተኛ አካል በተደረገ ጥናት ፌስቡክ ከ13 እመት በታች የሆኑ ህጻናት በወላጆቻቸው ከተፈቀዱላቸው ሰዎች ውጭ መልዕክት እንዲለዋወጡ መፍቀዱን መረገገጡም ነው የተገለጸው።
“ይህም ታዳጊዎችን አደጋ ላይ ጥሏል፤ ሜታም ለዚህ ጉዳይ ፈጣን ምላሽ መስጠት አለበት” የሚል መግለጫን ኮሚሽኑ ማውጣቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
ፌስቡክ ወላጆች “ሜሴንጀር ኪድስ” የሚጠቀሙ ልጆቻቸውን የሚቆጣጠሩበትን ስርአት ማስተካከል እንደሚገባውና የመረጃ ደህንነታቸውን እንዲያስጠብቅም አሳስቧል።
ሜታ ምላሽ እስከሚሰጥና የቀረበበትን ክስ እስኪያስተካክል ግን የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰዱበትም ነው ኮሚሽኑ ምክረሃሳብ ያቀረበው።
ኩባንያው ከታዳጊና ህጻናት መተግበሪያዎቹ በማስታወቂያ የሚያገኘው ገቢ ይቋረጥ የሚለው ቀዳሚው ነው።
ማስተካከያ እስኪያደርግ ድረስ አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ይፋ ከማድረግ ይቆጠብ ዘንድ የሚጠይቀውም ሌላኛው በኮሚሽኑ የቀረበ ምክረሃሳብ ነው።
የቴክኖሎጂ ኩባንያው ቃልአቀባይ አንዲ ስቶን በሰጡት ምላሽ፥ የኮሚሽኑ ክስ “ፖለቲካዊ” ይዘት ያለው ነው በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
“እንደ ቲክቶክ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች በአሜሪካ ምድር በነጻነት እየሰሩ” ሜታ ተነጥሎ የሚከሰስበት ምክንያት የለም ያሉት ቃልአቀባዩ፥ የቀረቡት ወቀሳና ክሶችን አንቀበላቸውም ብለዋል።
የአሜሪካ የንግድ ኮሚሽን ካምብሪጅ አናሌቲካ ከ10 ሚሊየን በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ ይዟል የሚለው መረጃ ከወጣበት ከ2018 ጀምሮ ምርምራ እያደረገ ይገኛል።
በዚህ ምርመራም እንደ ፌስቡክ ያሉ በሜታ የተጠቃለሉ ኩባንያዎች ተደጋጋሚ ቅሬታና በፍትሃዊነት እንታይ ጥያቄ ሲያነሱ ይደመጣል።
ኮሚሽኑ ግን “ፌስቡክ በተደጋጋሚ የሚገባውን ቃል አይፈጽምም፤ የተጠቃሚዎቹን መረጃ ደህንነት ማረጋገጥና ታዳጊዎችን የመጠበቅ ሃላፊነቱን አልተወጣም” ሲል ይከሰዋል።