የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ ገቢ በግማሽ ቀን ውስጥ 28 ቢሊዮን ዶላር ጨመረ
የሜታ ኩባንያ መስራች እና ስራ አስኪያጁ ገቢው የጨመረው የድርጅቱ አክስዮን ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ ነው
ሜታ ኩባንያ ለባለአክስዮኖች ትርፍ እንደሚያከፋፍል በገለጸ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የድርጅቱ አክስዮን ዋጋ አሻቅቧል
የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ ገቢ በግማሽ ቀን ውስጥ 28 ቢሊዮን ዶላር ጨመረ፡፡
አሜሪካዊው የቴክኖሎጂ ኩባንያ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ ከ140 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሀብት በመያዝ የዓለማችን አራተኛው ባለጸጋ ነው፡፡
ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ዋትስ አፕ እና ትሪድስ የተሰኙ የማህበራዊ ትስስር መተግበሪያዎችን በማበልጸግ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም አህጉራት በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች አሉት፡፡
ሁሉንም ድርጅቶቹን በሜታ ኩባንያ ስር ባንድ ላይ እያስተዳደረ የሚገኘው መስራቹ እና ስራ አስኪያጁ ማርክ ለባለአክስዮኖች ዓመታዊ የትርፍ ክፍፍል እንደሚሰጥ ይፋ ባደረገበት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የድርጅቶቹ አክስዮን ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ማርክ ዙከርበርግ በግማሽ ቀን ውስጥ 28 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ሀብት ማግኘቱን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የሜታ ኩባንያ አክስዮን ዋጋ የ20 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ማርክ ዙከርበርግ ደግሞ በዚህ ኩባንያ ውስጥ የ350 ሚሊዮን አክስዮን እንዳለው ተገልጿል፡፡
ዙከርበርግ በየዓመቱ ከኩባንያው አክስዮን ሽያጭ የተጣራ 700 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ላይ ነው የተባለ ሲሆን ለባለ አክስዮኖች ትርፍ ክፍፍል እከፍላለሁ ማለቱ የአክስዮን ገበያን በማናር ያልተፈለገ ውድድር እንዲኖር አድርጓል በሚል ትችቶችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
ፌስቡክ ህጻናት እና ወጣቶችን ለአደጋ አጋልጧል በሚል ከሰሞኑ ለቀረበበት ክስ ይቅርታ የጠየቀው ማርክ ዙከርበርግ በቀጣይ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል፡፡