ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በክፍያ ሰማያዊ ባጅ መስጠት ጀመሩ
የሜታ ኩባንያ እህት ኩባንያዎቹ በብሪታንያ ነው የሰማያዊ የማረጋገጫ ምልክቷን በክፍያ መስጠት የጀመሩት
ሜታ የክፍያ የሰማያዊ ባጅ አገልግሎቱን በአሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ መጀመሩ ይታወሳል
ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በብሪታንያ የሰማያዊ ባጅ ወይም ቨሪፊኬሽን በክፍያ መስጠት ጀመሩ።
በፌስቡክ እና ኢንስታግራም ላይ ተጠቃሚዎች የትክክለኛ አካውንት ማረጋገጫ ምልክቷን በወርሃዊ 9 ነጥብ 99 ዶላር ነው ማቅረብ የጀመረው።
ከ18 አመት በላይ እድሜ ያላቸውና የመንግስት መታወቂያ ማቅረብ የሚችሉ ብሪታንያውያን ሰማያዊ ባጁን ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።
ሜታ በአሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ አገልግሎቱን ቀደም ብሎ ማስጀመሩ የሚታወስ ነው።
ከስድስት ወራት በፊት ከ11 ሺህ በላይ ሰራተኞቹን ያሰናበተው ሜታ የክፍያ የሰማያዊ ባጅ አገልግሎቱ ገቢውን እንደሚያሳድግለት ይታመናል።
ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን የሚያገኙ አካላትም በድጋሚ በማመልከት በክፍያ ሰማያዊ ባጁን ማስቀጠል እንደሚችሉ ኩባንያው መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።
የኤለን መስኩ ትዊተር በህዳር ወር 2022 በወርሃዊ ክፍያ የማረጋገጫ ሰማያዊ ምልክቷን መስጠት መጀመሩ አይዘነጋም።
ትዊተር ከዚህ ቀደም ለታዋቂ ሰዎች፣ ፖለቲከኞች እና መገናኛ ብዙሃን ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በክፍያ ማስጀመሩ በመስክ ላይ ትችት ማስከተሉ ይታወሳል።
ክፍያውን መፈጸም ያልቻሉ አካላትን ሰማይዊ ባጅ ማንሳት መጀመሩም የአለም ሁለተኛውን ባለጠጋው ኩባንያ እና የትዊተር አካውንት ባለቤቶቹን ሲያነታርክ ሰንብቷል።
እንደ ሂላሪ ክሊንተን ያሉ የአሜሪካ ጉምቱ ፖለቲከኞች ሰማያሚ የማረጋገጫ ምልክት መነሳቱ ተመሳሳይ እና አሳሳች አካውንቶች በፍጥነት እንዲከፈቱ ማድረጉ ነው የተነገረው።