ሜታ 50 ሺህ ኪሎሜትር የሚረዝም የኢንተርኔት ገመድ በውቅያኖስ ውስጥ ሊዘረጋ ነው
የአለማችን ረጅሙ የኢንተርኔት ገመድ አሜሪካ፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ብራዚልን የሚያገናኝ መሆኑን ኩባንያው ገልጿል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/18/273-124049-meta-to-link-world-with-longest-subsea-cable_700x400.jpg)
95 በመቶ የሚሆነው የአለማችን የኢንተርኔት ዝውውር የሚከናወነው በውቅያኖስ ውስጥ በተዘረጉ ገመዶች አማካኝነት ነው
ሜታ የአለማችን ረጅሙን የኢንተርኔት ገመድ በውቅያኖስ ውስጥ ሊዘረጋ መሆኑን አስታወቀ።
"ፕሮጀክት ዋተርወርዝ" የሚል ስያሜ የተሰጠው 50 ሺህ ኪሎሜትር የሚረዝም ገመድ ተዘርግቶ ሲጠናቀቅ አምስት አህጉራትን ያገናኛል ተብሏል።
የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ባለቤቱ ሜታ ባወጣው መግለጫ ፕሮጀክቱ አሜሪካ፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ብራዚልን ጨምሮ ሌሎች ሀገራትን የሚያገናኝ መሆኑን ገልጿል።
ረጅሙ በውቅያኖስ ስር የሚዘረጋ የኢንተርኔት ገመድ ከዚህ ቀደሞቹ ባለስምንት እና 16 ጥንድ ፋይበሮች በላቀ ባለ24 ፋይበር መሆኑ ፈጣን ኢንተርኔት ለማድረስ እንደሚያስችልም ነው የጠቆመው።
አምስት አህጉራትን የሚያገናኘው "ፕሮጀክት ዋተርወርዝ" የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) መሰረተ ልማትን ለመደገፍ አይነተኛ ድርሻ ይኖረዋል።
"ፕሮጀክቱ አሜሪካ፣ ህንድ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በዋናዋና ክፍለአለማት ፈጣን ኢንተርኔት ለማዳረስ ያግዛል፤ ታላቅ የምጣኔ ሀብት ትስስር በመፍጠር የዲጂታል አካትችነትን ያፋጥናል"ም ነው ያለው ሜታ በመግለጫው።
"ዋተርወርዝ" እንደ ህንድ ባሉ በዲጂታል መሰረተልማት ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ በሚገኙ ሀገራት የዲጂታል ኢኮኖሚ እቅዳቸውን በፍጥነት ለማስፈጸም እንደሚረዳም አብራርቷል።
ሜታ ግዙፉ ፕሮጀክት ተጀምሮ የሚጠናቀቅበትንም ሆነ የተመደበለትን በጀት ግን አልጠቀሰም።
ቢሊየነሩ ማርክ ዙከርበርግ የሚመራው ተቋም ከ20 በላይ በሚሆኑ የውቅያኖስ ውስጥ የኢንተርኔት ገመድ ዝርጋታ ስራዎች ላይ መሳተፉን ይፋ አድርጓል።
95 በመቶ የሚሆነው የአለማችን የኢንተርኔት ዝውውር የሚከናወነው በውቅያኖስ ስር በተዘረጉ ገመዶች አማካኝነት ነው ይላል የዘጋርዲያን ዘገባ።
ገመዶቹ ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው፤ ሀገራት በጦርነት ውጥረት ውስጥ ሲገቡ የጥቃት ኢላማ ሊያደርጓቸው ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች ተደጋግመው ሲነሱ ይደመጣል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ባለፈው አመት በባልቲክ ባህር ስር በተዘረጉ ገመዶች ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ በመርከቦች ላይ የሚደረገውን ክትትል የሚያጠናክር ተልዕኮ መጀመሩ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት 600 የሚሆኑ የኢንተርኔት ገመዶች ከውቅያኖስ ስር እንደሚገኙ ቴሌጄኦግራፊ የተባለው የጥናት ተቋም መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህ መካከል ሶስት አህጉራትን የሚያገናኘው "2አፍሪካ" የተባለው 45 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝም የኢንተርኔት ገመድ ተጠቃሽ ነው።
ጉግል ባለፈው አመት አፍሪካ እና አውስትራሊያን የሚያገናኝና 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ገመድ በፓሲፊክ ውቅያኖስ ስር እንደሚዘረጋ ማስታወቁ ይታወሳል።