የዴሞክራቶች ደጋፊ የነበረው ማርክ ዙከርበርግ ከትራምፕ ጋር ተገናኘ
ዙከርበርግ ከ2021ዱ የካፒቶል አዳራሽ ነውጥ በኋላ የትራምፕን የፌስቡክና ኢንስታግራም ገጾች ለሁለት አመት መዝጋቱ ይታወሳል
ሜታ የፌስቡክ መስራቹ በፍሎሪዳ የትራምፕ መኖሪያ ቤት ተገኝቶ ከተመራጩ ፕሬዝዳንት ጋር እራት መመገቡን አረጋግጧል
የሜታ ስራ አስፈጻሚው ማርክ ዙከርበርግ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር መገናኘቱ ተነገረ።
ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕን ያጣመረው ሜታ ሃላፊው በፍሎሪዳ በሚገኘው የትራምፕ ቅንጡ መኖሪያ ቤት "ማራ ላ ጎ" በመገኘት ከትራምፕ ጋር እራት መመገቡን ኩባንያው አረጋግጧል።
የሜታ ቃልአቀባይ ዙከርበርግ ከትራምፕ የእራት ግብዣው እንደደረሰውና ከተመራጩ ፕሬዝዳንት እጩ የካቢኔ አባላት ጋር በመገናኘቱ ምስጋናውን እንደሚያቀርብ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ኒውዮርክ ታይምስ ግን ከትራምፕ ጋር ለመገናኘት ጥያቄውን ያቀረበው ዙከርበርግ መሆኑን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
የዴሞክራቶች ደጋፊው ማርክ ዘከርበርግ እና ትራምፕ ከጥር 6 2021 የካፒቶል አዳራሽ ነውጥ በኋላ ግንኙነታቸው ይበልጥ ሻክሯል።
ትራምፕ ግጭት የሚቀሰቅሱ መልዕክቶችን በፌስቡክና ኢንስታግራም ገጻቸው ላይ አጋርተዋል በሚልም ለሁለት አመት ታግደው በ2023 እንደከፈተላቸው የሚታወስ ነው።
ዙከርበርግ በ2020 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዴሞክራቶች መራጮች በብዛት ለሚገኙባቸው ተቋማት 400 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን አሳይቷል።
በምርጫው ባይደን እንዲያሸንፉም ፌስቡክ ትልቅ ሚና መጫወቱን ትራምፕ በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ተደምጠዋል።
ትራምፕ በጥቅምት ወር 2024 ባደረጉት ቃለምልልስ ግን ከ35 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን ያፈሩበትን የፌስቡክ አካውንታቸውን ለሁለት አመት የዘጋባቸው ዙከርበርግ ከቀድሞው የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።
የፍሎሪዳው የእራት ግብዣም የሻከረውን ግንኙነት እንዳለዘበ ቢነገርም የመከሩባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ግን አልተጠቀሱም።
ተንታኞች ግን ዙከርበርግ ከትራምፕ ጋር እራት ለመመገብ ወደ ፍሎሪዳ ያቀናው የቴክኖሎጂ ተቀናቃኙ ኤለን መስክ በትራምፕ የተሰጠውን ልዩ ስፍራ ለመገዳደር ነው ይላሉ።
የሜታው ስራ አስፈጻሚ እንደ መስክ ሹመት ባያገኝ እንኳን ተመራጩን ፕሬዝዳንት መወዳጀት ዝቅ እያለ ገቢውን ለመታደግ ያግዘዋል።
የቴስላ እና ኤክስ ስራ አስፈጻሜው ኤለን መስክ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆናቸው በተበሰረበት እለት አጠቃላይ ሃብቱ በ20 ቢሊየን ዶላር ጨምሯል።
በአንጻሩ የሜታ ስራ አስፈጻሚው ማርክ ዙከርበርግ ትራምፕ ከተመረጡ ወዲህ ከ3 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ ማጣቱ ተገልጿል።