የብረት አቅርቦት መቀነስ የጦር መሳሪያ አምራቾችን እየፈተነ ነው
የጀርመኑ ሊዮፓርድ 2 ታንክ አምራች ኩባንያ በብረት አቅርቦት ምክንያት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን በፍጥነት ማድረስ አልቻልኩም ብሏል

ብሪታንያ ከፈረንሳይ ብረት ለማስገባት ብቻ 40 ቢሊየን ዶላር አውጥታለች
የብረት አቅርቦት የጦር መሳሪያ አምራቾችን እየፈተነ መሆኑ ተነግሯል።
ከአሜሪካ በመቀጠል ከፍተኛ ወታደራዊ በጀት በምትመድበው ብሪታንያ የብረት ኢንዱስትሪዎች ምርታማነት ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ ነው።
ለንደን ለባህር ሰርጓጅ መርከቦች ግንባታ የሚውሉ ብረቶችን ከፈረንሳይ ለማስገባት 40 ቢሊየን ዶላር መክፈሏንም መረጃዎች ያሳያሉ።
በጀርመንም ይሄው የብረት አቅርቦት ችግር አሳሳቢነቱ መጨመሩን “ኬኤንዲኤስ” የተሰኘው የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያ ገልጿል።
ሊዮፓርድ 2 የተሰኙትን ታዋቂ ታንኮች የሚሰራው ይህ ኩባንያ፥ 200 አመት እድሜ ያለውን የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ 80 በመቶ ድርሻ መግዛቱንም ነው ወልስትሪት ጆርናል ያስነበበው።
“ኬኤንዲኤስ” ጀርመን ለዩክሬኑ እንድትሰጥ ስትወተወት የቆየችለትን ታንክ የሚያመርት ነው የሚለው ዘገባው፥ ይሁን እንጂ ታንኩን ለማምረት ወሳኝ የሆነው የብረት አቅርቦት ፈተና ሆኖብኛል ማለቱን ያክላል።
ኩባንያው ከታንክ ባሻገር ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ወደ ኬቭ በመላክ ላይ እንደሚገኝም ይጠቅሳል።
የብረት አቅርቦት ጉዳይ ምዕራባውያን የቻይና እና ሩሲያን ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለመግታት ለሚያደርጓቸው የእጅ አዙር ፍልሚያዎች ስጋት ሳይደቅን አልቀረም።
የአሜሪካ እና የአውሮፓ መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ስራ አስፈጻሚዎችም ብረት አቅራቢዎች በቁጥር ጥቂት ናቸው፤ የታዘዙትን የሚያደርሱትም ረጅም ጊዜ ወስደው ነው ይላሉ።
ይህም የጦር መሳሪያዎች በፍጥነት እንዳይደርሱና ዋጋቸውም በየጊዜው እንዲጨምር ማድረጉንም ይናገራሉ ይላል ወልስትሪት ጆርናል።
ለዚህም ለአብነት የሚነሳው የዩክሬኑ ጦርነት ነው። ኬቭ ከምዕራባውያኑ ከተገባላት የጦር መሳሪያ ድጋፍ የደረሳት እጅግ ጥቂቱ መሆኑ ይነገራል። በዚህም ምክንያት ከአንድ ወር በፊት የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት መንቀራፈፉን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጭምር ሲናገሩ ተደምጧል።
የጀርመኑ ታንክ አምራች ኩባንያ (ኬኤንዲኤስ) ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ጀምሮ የጀርመንን የኢንዱስትሪ አብዮት ያገዘው “ፍሬደሪክ ዊልሄልም ሁቴ”ን 80 በመቶ ድርሻ መግዛቱም ይህን ችግር ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
የብረት ማቅለጫ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ ሜትሪክ ቶን “ባለስቲክ ብረት” (እጅግ ጠንካራ ብረት) ያመርታል፤ በቀጣይ አመት ደግሞ ምርቱን በእጥፍ ለማሳደግ አቅዷል።
ይህም በተለያዩ ሀገራት በሚደረጉ ጦርነቶች ታንኮችና ወታደትራዊ ተሽከርካሪዎችን በፍጥነት ለማቅረብ ያግዘዋል ነው የተባለው።