ማይክሮሶፍት ከ11 ሺህ በላይ ሰራተኞቹን ሊቀንስ እንደሆነ ተገለጸ
ኩባንያው በሰው ሃብት አስተዳደርና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የሚገኙ የስራ እርከኖችንም ሊያጥፍ መሆኑ ተገልጿል
ማይክሮሶፍት፥ አማዞን፣ ሜታ እና ትዊተርን በመከተል ሰራተኞቹን የሚቀንስ ግዙፍ ኩባንያ ሆኗል
ማይክሮሶፍት ከ11 ሺህ በላይ ሰራተኞቹን ሊቀንስ እንደሆነ ተገለጸ።
የኮምፒውተር እና ሶፍትዌሮች አምራች ኩባንያ ማይክሮሶፍት ኮርፖሬሽን የሰራተኞቹን ቁጥር ሊቀንስ መሆኑ እየተዘገበ ነው።
የአሜሪካው ኩባንያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቹን የሚቀንሰው ተጠባቂ የእድገት ጉዞው አዝጋሚ ስለሆነበት ነው ተብሏል።
ከ221 ሺህ በላይ የሙሉ ጊዜ ሰራተኞች ያሉት ማይክሮሶፍት ከጠቅላላው ሰራተኛ አምስት በመቶውን ከስራ ለማሰናበት ማቀዱን የብሪታንያው ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
ይህም ከ11 ሺህ በላይ የኩባንያው ሰራተኞች በዚህ ሳምንት መቀነሳቸው እንደማይቀር ያሳያል ያለው ዘገባው፥ ይህም በኩባንያው ታሪክ ከፍተኛው የሰራተኛ ስንብት መሆኑን ጠቁሟል።
ኩባንያው በሰው ሃብት አስተዳደርና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የሚገኙ የስራ እርከኖችንም ሊያጥፍ መሆኑን ብሉምበርግ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
ማይክሮሶፍት ግን እስካሁን በጉዳዩ ላይ ማረጋገጫ አልሰጠም።
ኩባንያው አለም በኮሮና ምክንያት በገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የኮምፒውተርም ሆነ የሶፍትዌር ንግዱ በሚፈለገው ፍጥነት አልሄደለትም ነው የተባለው።
በዚህም የሰራተኞቹን ቁጥር እንዲቀንስ ከፍተኛ ጫና ሲደረግበት መቆየቱን ነው ሬውተርስ ያስነበበው።
በጥቅምት ወር 2022 ከ1 ሺህ በላይ ሰራተኞችን የስራ ውል ማቋረጡን የሚጠቅሱ ዘገባዎችም ሲወጡ የነበረ ቢሆንም፥ ማይክሮሶፍት ማረጋገጫ አልሰጠም።
የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸውን በቋሚነት እና በጊዜያዊነት ከስራ በማሰናበት ወጪያቸውን ለመቀነስ ጥረት እያደረጉ ነው።
አማዞን፣ የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ እና ትዊተር ሰራተኞቻቸውን ከቀነሱ ኩባንያዎች መካከል ይጠቀሳሉ።