ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ለሰራተኞቻቸው ምን ያህል ደመወዝ እንደሚከፍሉ ያውቃሉ?
አፕል ባለፈው አመት ብቻ ከቴክኖሎጂእና አገልግሎት ሺያጭ 95 ቢሊዮን ዶላር ወደ ካዝናው አስገብቷል
ሜታ ኩባኒያ ለሰራተኞቹ በአመት እስከ 335ሺህ ዶላር በመክፈል ከቴክኖሎጂ ኩባኒያዎች ቀዳሚው ነው
ጎግልን ጨምሮ እንደ አፕል የመሳሰሉ የዓለማችን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባኒያዎች ለሰራተኞቻቸው ዳጎስ ያለ የደመወዝ መጠን እንደሚከፍሉ ይነገራል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይደር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን የደመወዝ መረጃ በመመርመር ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በየአመቱ ምን ያህል እንደሚከፍሏቸው የሚያመለክት መረጃ በዚህ ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይደር ኤርባብን፣ አማዞንን፣ አፕልን፣ ፌስቡክን፣ ጎግልን፣ ማይክሮሶፍትን፣ ሴልስፎርስን ፣ ስናፕ እና አበርን ጨምሮ ቁጥሮቹን የተነተነ ሲሆን ፤ የቴክኖሎጂ ኩባኒያዎች ለሰራተኞቻቸው የሚከፍሉት የደመወዝ መጠንን በተመለከተ ይፋ ያደረገው መረጃ አበል እና ጉርሻ ሳይጨምር እንደሆነም ገልጿል፡፡
ጎግል
የጎግል ሶፍትዌር ኩባኒያ ለኢንጂነሮቹ የሚከፍለው ክፍያ በአመት ከ300 እስከ 353 ሺህ ዶላር ሊደርስ ይችላል፡፡ የኩባኒያው ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ምክትል ፕሬዘዳንት ዓመታዊ ደመወዝ 475 ሺህ ዶላር እንደሆነም የቢዝነስ ኢንሳይደር መረጃ ያሳያል።
ጎግል እንደ አማዞን ዌብ ሰርቪስ እና ማይክሮሶፍት ኮርፖሬሽን ካሉ ትልልቅ ተፎካካሪዎች ጋር ራሱን ለማስተካከል የሰው ሃይል አቅሙ እጅጉን እያጠናከረ መሆኑም በመረጃው ተመላክቷል፡፡
አማዞን
የአማዞን ክላውድ ሶሉሽንስ ኢንጂነሮች እንደየ የስራ አካባቢው እና ችሎታቸው በአመት ከ90 ሺህ 800 እስከ 185 ሺህ ዶላር ያገኛሉ።
አፕል
በአፕል ኩባኒያ ወስጥ የሚሰሩ ከፍተኛ የማርኬቲንግ ባለሙያዎች በዓመት እስከ 325 ሺህ ዶላር ይከፈላቿል፡፡
ኩባኒያው ባለፈው አመት እድገት የ33% ዳጎስ ያለ የትርፍ ያገኘ ሲሆን ከአይፎን፣አይፓድ፣ ማክስ እና ሌሎች መሳሪያዎች እንዲሁም ከአገልግሎቶች ሽያጭ 95 ቢሊዮን ዶላር ወደ ካዝናው ማስገባት ችሏል።
ተንታኞች 1 ትሪሊዮን ዶላር እና 2 ትሪሊየን ዶላር በማድረስ የመጀመሪያው መሆን የቻለው ኩባንያ በዚህ አመት 3 ትሪሊዮን ዶላር የገበያ ካፒታላይዜሽን በማድረስ የመጀመሪያው ኩባንያ ለመሆን በመንደርደር ላይ መሆኑም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
ዴል
የዴል ባለቤቶች የሰባት አሃዝ ደሞዝ የሚያገኙበት ሲሆን አብዛኛው የዴል ሰራተኞች ደመወዝ በስድስት አሃዝ ክልል ውስጥ ይገኛል፡፡
እንደ ቢዝነስ ኢንሳይደር መረጃ ከሆነ ኩባኒያው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ ባገኘበት ወቅት አንዳንድ ሰራተኞች 200 ሺህ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማግኘት ችለዋል፡
አይቢኤም
የአይቢኤም ሰራተኞች በዓመት እስከ 335ሺህ ዶላር ያገኛሉ፡፡
አሁን ላይ ኩባኒያው ወደ ክላውድ ኮምፒውቲንግ ዘርፍ በመስፋፋት እንዲሁም ሃርድዌር እና መሳሪያዎችን በማዘጋጀት ላይ ነው፡፡
አይቢኤም ወደ 350ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በአብዛኛው በክላውድ፣ሃይብሪድ ኮምፒዩቲንግ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የመሳሰሉ የኢንጂነሪነግ ተሰጥኦዎች ያሏቸው እንዲሁም እንደ ስትራቴጂ፣ አማካሪ እና የንግድ ትንተና ባሉ ዘርፎች ስፔሻላይዝ ያደረጉ ናቸው።
ኢንቴል
የኢንቴል ኢንጂነሮች በአመት ከ300 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ያገኛሉ፡፡ ያም ሆኖ ኩባኒያው አሁን ከታይዋን ሴሚኮንዳክተር፣ ኤኤምዲ፣ ንቪዳ እና ሌሎች ኩባኒያዎች ፉክክር እየገጠመው እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ሜታ
በሜታ ኩባኒያ የሚሰሩ ኢንጂነሮች እንደየሚሰሩበት አከባቢና የስራ ሁኔታ በየአመቱ ወደ 360 ሺህ ዶላር የሚጠጋ ደመወዝ ይከፈላሉ፡፡
ለምሳሌ በካሊፎርኒያ የሚገኝ የመረጃ ተንታኝ በአመት ከ130 እስከ 150 ሺህ ዶላር ሲያገኝ በኒውዮርክ የሚገኝ የሶፍትዌር ኢንጂነር 160 ሺህ ዶላር ያገኛል፡፡