ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ለምን ወደ ሰራተኛ ቅነሳ አመሩ?
ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከ100 ሺህ ሰራተኞች ተቀንሰዋል ተብሏል
የሰራተኞች ቅነሳው በዓለም ቴክኖሎጂ እድገት ላይ ምን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል?
የዓለም ማህበረሰብ የዕለት ተዕለት ህይወት በማቅለል የሚታወቁት ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸውን በመቀነስ ላይ ተጠምደዋል፡፡
የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ እናት የሆነው ሜታ፣ ትዊትር፣ አማዞን፣ ፕራይም፣ ኔትፍሊክስ፣ ኮይን ቤዝ እና ሌሎችም ብዙ ሰራተኞቻቸውን ከቀነሱ የዓለም ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባያዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ደንበኞች እና ትርፍ እንደተንበሸበሹ ሲገልጹ የቆዩ ቢሆንም አሁን ላይ ወደ ሰራተኞች ቅነሳ ማምራታቸው ለብዙዎች አግራሞትን ፈጥሯል፡፡
በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ጥናቶችን እና ሌሎች መረጃዎችን በማውጣት የሚታወቀው ፎርብስ በድረገጹ ለምን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸውን እንዳባረሩ ጥናቱን ይፋ አድርጓል፡፡
እንደ ፎርብስ መረጃ ከሆነ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ ሰራተኞች ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተባረዋል፡፡
ሜታ፣ ትዊትር፣ አማዞን፣ ፕራይም፣ ኔትፍሊክስ፣ ኮይን ቤዝ እና ሌሎችም ሰራተኞቻቸውን ከቀነሱ የቴክኖሎጂ ኩባያዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ጎግል፣ ስፖቲፋይ፣ የቲዩብ፣ ሾፒፋይ፣ ስናፕ እና ሌሎች ኩባንያዎች በቀጣይ የሰራተኞች ቅነሳ ያደርጋሉ ተብለው ከሚገመቱ ኩባንያዎች መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑ ፎርብስ በዘገባው ገልጿል፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች ለምን ይሄን ያህል ሰራተኞች ሊቀንሱ ቻሉ? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ሲሆን ለዚህ ምልስ ይሆናሉ የተባሉ ሀሳቦችም ተዘርዝረዋል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት የኮሮና ቫይረስ መከሰት እና እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸው ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ትልቅ የምስራች የነበረ ሲሆን ኩባንያዎቹ የተጠቃሚዎች እና ትርፍ መብዛት ብዙ ሰራተኞች እንዲቀጥሩ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
ይሁንና አሁን ላይ ህይወት ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ ሲመለስ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተጠቃሚዎች ቁጥር ማሽቆልቆል ለኩባንያዎቹ ሰራተኞች መቀነስ ዋነኛው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት መከሰትን ተከትሎ የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ እና ዜጎች በተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ምክንያት ገንዘባቸውን ለመሰረታዊ ነገሮች በማዋላቸው የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ገቢ በመቀነሱ ሰራተኞቻቸውን ወደ መቀነስ እንዲያመሩ አድርጓቸዋል መባሉ ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡
ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች የሚገኙባቸው አውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ጦርነቱን ተከትሎ በቀጣይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አለመታወቁ እና የኢኮኖሚ ድቀት አይቀሬ በመሆኑ እነዚህ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተጨማሪ የስራ ቅነሳ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ተሰግቷል፡፡
እንዲሁም ብዙ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ከሰው ይልቅ አርቲፊሺያል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ መጠቀም መሸጋገራቸው ሌላኛው ለሰራተኞች መባረር ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ይህ ግዙፍ የዓለም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሰራተኞች መቀነስ በቴክኖሎጂ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል የተሰጋ ሲሆን በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ ያሉ የቴክኖሎጂዎች ስራዎች የበለጠ ሊጎዱ እንደሚችልም ዘገባው አክሏል፡፡