ማይክሮሶፍት ‘ዊንዶው 11’ የተሰኘ አዲስ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ይፋ አደረገ
ዊንዶውስ 11 የአንድሮይድ መተግበሪያዎች በዊንዶውስ ኮምፒውተሮች ላይ መጠቀም የሚያስችል ነው
ዊንዶውስ 11 ኦፕሬቲንግ ሲስተም ከዚህ ቀደም ዊንዶውስ 10 ለሚጠቀሙ በሙሉ በነጻ የሚቀርብ ይሆናል
ማይክሮሶፍት ኩባንያ አዲሱን አዲሱን ዊንዶውስ 11 መተግበሪያ ስርዓት (ኦፕሬቲንግ ሲስተም) በትናትናው እለት ይፋ አድርጓል።
አዲሱ ዊንዶውስ 11 ኦፕሬቲንግ ሲስተም የአንድሮይድ መተግበሪያዎች በዊንዶውስ ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች ላይ መጠቀም የሚያስችል ነው ተብሏል።
በተጨማሪም አዲሱ ኦፕሬቲንግ ሲስተም እንደ ማክ ያሉ ኮምፒውተሮች ላይ ከቤት ሆኖ መስራት የሚያስችል እና ጌሞችን በቀላሉ መጫወት የሚያስችሉ አገልግሎቶች በውስጡ አካቷል።
በዊንዶውስ 11 ኦፕሬቲንግ ሲስተም ከዚህ ቀደም በግራ በኩል የነበረው የ"Start" ቁልፍ በኮምፒውተራችን ስክሪኑ መሃል ላይ እንዲሆን መደረጉንም ኩባንያው አስታውቋል።
እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከደህንነት ጋር ተያይዘው ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎች በአዲሱ ዊንዶውስ 11 ኦፕሬቲንግ ሲስተም መፈታቱንም ነው ኩባንያው የገለጸው።
የአዲሱ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ቅድመ ምልከታ ለመተግበሪያ አልሚዎች በቀጣይ ሳምንት እንደሚለቀቅም ነው ማይክሮሶፍት ያስታወቀው።
ዊንዶውስ 11 ኦፕሬቲንግ ሲስተም ከዚህ ቀደም ዊንዶውስ 10 ለሚጠቀሙ በሙሉ በነጻ የሚቀርብ ሲሆን፤ የዊንዶውስ 10 ተጠቃሚዎች የኦፕሬቲንግ ሲስተማቸውን ወደ አዲሱ ዊንዶውስ 11 ማሻሻል ብቻ ነው የሚተበቅባቸው ተብሏል።
ነገር ግን አዲሱን ዊንዶውስ 11 ለማግኘት የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎቻችን ቢያንስ 64 ጊጋ ባይት ያህል ማከማቻ ቦታ (ሶቶሬጅ) እና 4 ጊጋ ባይት ራም ሊኖረው እንደሚገባም ነው የተገለጸው።
እንደ ማይክሮሶፍት መረጃ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ዊንዶውስ 10 ኦፕሬቲንግ ሲስተምን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ።
ኩባንያው ዊንዶውስ 10 በፈረንጆቹ 2015 ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፤ በወቅቱም ዊንዶውስ 10 የመጨረሻው ኦፕሬቲንግ ሲስተም መሆኑን በመጥቀስ፤ ከዚህ በኋላ አዲስ ይፋ አላደርግም ብሎ እንደነበረ አይዘነጋም።
ቆየት ብሎ ባወጣው መረጃ ደግሞ ዊንዶውስ 10 ኦፕሬቲንግ ሲስተም በአውሮፓውያኑ በ2015 የአገልግሎት ዘመኑ ያበቃል የሚል አስተያየትም ሰጥቷል።