ሴት ልጅ ሲወልዱ በነርሶች የሚያስገድሉት ሕንዳዊያን ወላጆች
ወላጆች አዋላጅ ነርሶች ሴት ህጻናትን እንዲገድሉላቸው የተለያዩ ስጦታዎችን ይሰጣሉ
በሕንዷ ቢሃር እና ሌሎች ግዛቶች ወንድ ልጅ ሲወለድ መንደሩ እና ቤተሰቡ በደስታ ይፈነድቃሉ
ሴት ልጅ ሲወልዱ በነርሶች የሚያስገድሉት ሕንዳዊያን ወላጆች
1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ህዝብ በመያዝ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለ ብዙ ህዝብ በሆነችው ሕንድ አያሌ እና ሌላውን ዓለም የሚያስገርሙ ክስተቶች ይካሄዱባታል፡፡
ከነዚህ መካከል በምስራቃዊ ሕንድ ያሉ ግዛቶች ሴት ልጅ መውለድን እንደ መጥፎ እድል የሚያዩ ሲሆን በተቃራኒው ወንድ ልጅ ሲወለድ ደግሞ ወላጆችን ጨምሮ ቤተሰቡን ያስደስታል፡፡
ይህ አመለካከት መነሻው የጋብቻ ባህል ሲሆን በምስራቃዊ ሕንድ አካባቢዎች ጋብቻ ሲመሰረት የሴት ቤተሰቦች ለወንዱ ወይም ባልየው ቤተሰቦች ስጦታ መስጠት ግዴታ ስለሆነ ነው፡፡
በዚህ ባህል መሰረት ብዙ ሴት ልጆችን የሚወልዱ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ሲድሩ ለሙሽራው ቤተሰቦች ስጦታ መስጠት ግዴታ ስለሚሆን ያላቸውን ንብረት በሙሉ ለስጦታ እንዲሰጡ ይገደዳሉ፡፡
ያላቸውን ንብረቶች በስጦታ መልክ መስጠት የሚፈሩ ወላጆች ሴት ልጅ ሲወልዱ ወዲያውኑ ከአዋላጅ ነርሶች ጋር በመነጋገር እንድትገደል አልያም በጫካ ውስጥ መጣል የተለመደ ክስተት ነው፡፡
በአንጻሩ ወንድ ልጅ ሲወለድ እንደ ጥሩ እድል እና ስጦታ እንደሚያመጣ ስለሚታሰብ ገና ሲወለድ ጀምሮ በደስታ የማደግ እድል አለው፡፡
ወላጆች ሴት ልጆችን ሲወልዱ ለአዋላጅ ነርሶች ጉቦ በመስጠት አልያም በማስፈራራት ህጻናቱን እንዲገደሉ ማድረጋቸውን ተከትሎ በምስራቃዊ ሕንድ ያሉ ወንዶች ቁጥር ከሴቶች አንጻር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሕንድ ሚስቱ የማገጠችበት ባል የፈጸመው ድርጊት አነጋገረ
እንደዚህ ዘገባ ከሆነ አዋላጅ ነርሶች ሴት ህጻናትን እንዲገድሉ የሚገደዱ ሲሆን ይህን መፈጸም ካልቻሉ ደግሞ ወላጆች በራሳቸው ወይም በቤተሰባቸው ላይ ጥቃት እንደሚያደርሱ ያስጠነቅቋቸዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ነርሶች የሚደርስባቸውን በመፍራት አልያም የሚያገኙትን ጥቅም በማሰብ ሴት ህጻናትን እንደተወለዱ ይገድሏቸዋል፡፡
ክስተቱ በስፋት በሚፈጸምባት በቢሃር ግዛት ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነርሶች አሉ የተባለ ሲሆን ከዚህ በፊት በተሰራ ጥናት አንድ ነርስ በአማካኝ ከ15-30 ሴት ህጻናትን ይገድላሉ፡፡
ክስተቱ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም የሀገሪቱ መንግስት ድርጊቱ ህገወጥ መሆኑን እና ቅጣት እንደሚያስከትል ከ1965 ጀምሮ ህግ ቢያወጣም አሁንም አልቆመም፡፡
ድርጊቱን ለማስቆም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በስፋት እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ነርሶች ሴት ህጻናትን ከመግደል ይልቅ በማደጎ ወደ ሌላ አካባቢዎች እንዲወሰዱ ከማድረግ ጀምሮ በማህበረሰቡ ላይ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ በጋራ እየሰሩ ናቸው ተብሏል፡፡