በችሎታቸው የተመረጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ሊገነቡ ነው
በልህቀት ማዕከልነት እንደሚያገለግሉም ነው የተገለጸው
ትምህርት ቤቶቹ የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ የሚኒስትሪ ተፈታኞች የሚማሩባቸው ናቸው ተብሏል
በችሎታቸው የተመረጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው 50 ትምህርት ቤቶች በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች ሊገነቡ እንደሆነ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ትምህርት ቤቶቹ የ8ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱና በችሎታቸው የተመረጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው እንደሚሆኑ ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ገጹ አስታውቋል።
ከሚኒስቴሩ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በሁሉም ክልሎች በአይነታቸው የተለዩና የልህቀት ማዕከል የሚሆኑ 50 ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ ብለዋል።
ትምህርት ቤቶቹ ቀጣይ የአገር መሪ የሚሆኑ ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎች የሚፈልቁባቸው፣ በችሎታቸው ብቻ የሚመረጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶቹ የ8ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ውጤትን መሠረት ባደረገ የትምህርት ሚኒስቴር የሚያወጣውን መመዘኛ የሚያሟሉ ተማሪዎች የሚማሩባቸው ናቸው እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ።
የልህቀት ማዕከላቱ ከሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች የሚመለመሉ ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያስተምሩ እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዲያስፓራ ትረስት ፈንድ በ3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር 4 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ከሚኒስቴሩ ጋር ማድረጉ ተሰምቷል፡፡