“ሚስ ዩኒቨርስ” 2019
ደቡብ አፍሪካዊቷ ዞዚቢኒ ቱንዚ የዘንድሮውን የ 2019ን “ሚስ ዩኒቨርስ” የቁንጅና ውድድር አሸንፋ ትናንት ህዳር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. የክብር ዘውዷን ደፍታለች፡፡ ዘውዱን ያስቀመጠችላት የ2018 ሚስ ዩኒቨርስ አሸናፊ ፊሊፒናዊቷ ካትሪኦና ግሬይ ናት፡፡
ዞዚቢኒ በተለያዩ ዙሮች ላይ ባደረገቻቸው አልባሳት ዳኞችንና አድናቂዎቿን እጅግ በማስደመም ነው ውድድሩን ያሸነፈችው፡፡
“እኔን የሚመስሉ-የኔን አይነት ቆዳ እና ጸጉር ያላቸው ሴቶች በፍጹም ቆንጆ ተብለው በማይታዩበት አለም ነው ያደግኩት፡፡” ስትል ዞዚቢኒ ቱንዚ ሽልማቷን በተረከበችበት ወቅት ተናግራለች፡፡ “አሁን ይህ አስተሳሰብ የሚያበቃበት ጊዜ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ህጻናት እኔን እንዲያዩኝ እና የፊታቸውን ነጸብራቅ በፊቴ እንዲያዩት እፈልጋለሁ፡፡” ስትልም ላደገችበት ማህበረሰብ ቀጣይ ትውልድ መልእክት አስተላልፋለች፡፡
በጥያቄና መልስ ጊዜዋ ሴት ልጆች በዋናነት መሪነትን መማር አለባቸው በማለትም የ “ሚስ ዩኒቨርስ” 2019 አሸናፊዋ ደቡብ አፍሪካዊት ቆንጆ ተናግራለች፡፡
የዞዚቢኒ ቱንዚ ዋነኛ ተፎካካሪ የነበሩት የፖርቶ ሪኮ ሚስ ማዲሰን አንደርሰን እና ሚስ ሜክሲኮዋ ሶፊያ አራጎን በ “ሚስ ዩኒቨርስ” 2019 በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን