መሃመድ ቢን ዛይድ እና አል ቡርሃን በሁለትዮሽ ግንኙነቶች እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ተወያዩ
ዩኤኢ በሱዳን ሰላም ፣ መረጋጋት እና ዕድገት እንዲኖር የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ ሼህ መሃመድ ገልጸዋል
ሼህ መሃመድ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ቀውሶችን ለመፍታት ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ስለመሆኑ በአፅንዖት አንስተዋል
ትናንት እሁድ እለት የአቡዳቢ ዘውዳዊ ልዑል እና የዩኤኢ መከላከያ ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼህ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ፣ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የሱዳንን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የዩኤኢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የፕሬዚዳንት ጉዳዮች ሚኒስትር ሼህ መንሱር ቢን ዛይድ አል ናህያን የተገኙ ሲሆን ፣ ዩኤኢ ለሱዳን ስለምታደርገው ድጋፍ አል-ቡርሃን አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ አካላት በውይይታቸው በሀገራቱ የጋራ ጉዳዮች በተለይም በአፍሪካ ቀንድ እና በምስራቅ አፍሪካ ዙሪያ ሀሳብ ተለዋውጠዋል ፡፡
ከአፍሪካ ቀንድ ጋር በተያያዘም ውዝግቦችን እና ቀውሶችን ለማብረድ እና ለተፈጠሩ አለመግባባቶች መፍትሔ ማምጣት ለውይይት ቅድሚያ መስጠት እና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎችን መፈለግ አስፈላጊ ስለመሆኑ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ፣ የሱዳን መረጋጋት እና ደህንነት ለቀጣናው ደህንነት አንድ ወሳኝ ምሰሶ መሆኑን በማመን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሱዳን ሰላም ፣ መረጋጋት እና ዕድገት እንዲኖር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል፡፡
አል-ቡርሃን በበኩላቸው ሱዳን ከሁለቱን ሀገራት እና ህዝቦቻቸው ታሪካዊ ግንኙነት አንፃር ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተለያዩ የትብብር ዘርፎችን ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ነው የገለጹት፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት ሊቀመንበር አል ቡርሃን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዩኤኢ የገቡት በትናንትናው ዕለት ነው፡፡