“ሱዳን የግድቡን ጉዳይ ከድንበር ጋር የማስተሳሰር ፍላጎት አላት ሆኖም ሁለቱም የተለያዩ ናቸው”-አምባሳደር ዲና
ሱዳን የግድቡ ጉዳይ በህብረቱ በኩል ይፈታ እና ተጨማሪ አደራዳሪዎችን እንፈልጋለን የሚሉ ሁለት የተለያዩ አቋሞች እንዳሏትም ነው የተናገሩት
ቃል አቀባዩ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በተያያዘ “የይገባኛል ጥያቄ ማንሳቷ አስነዋሪ ነው”ም ብለዋል
ሱዳን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በተያያዘ የይገባኛል ጥያቄ ማንሳቷ አስነዋሪ ድርጊት መሆኑን ኢትዮጵያ አስታወቀች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ በመስጠት ላይ ናቸው።
አምባሳደር ዲና በዚህ ጊዜ እንዳሉት የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ውሀ እና የኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የተለያየ አቋም በማራመድ ላይ ናቸው ብለዋል።
የህዳሴውን ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲፈታ እንፈልጋለን እና ተጨማሪ አደራዳሪዎች በድርድሩ ይሳተፉ የሚሉ ሁለት የተለያዩ አቋሞች በሱዳን በኩል እየተንጸባረቁ መሆኑን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
ግድቡን ከድንበር ጋር የማስተሳሰር ፍላጎት በሱዳን በኩል አለ ያሉት አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ ሁለቱም ጉዳዮች የተለያዩ መሆናቸውን እና ችግሮቹን በድርድር መፍታት ትፈልጋለች ብለዋል።
ሱዳን ቤንሻንጉል ጉሙዝ የእኔ ነው በሚል ያነሳችው ጉዳይ አስነዋሪ መሆኑንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አክለው ያነሷቸው ጉዳዮች ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ በተያዘለት ጉዜ እንዲካሄድ ሁሉም ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት 15 ቀናት በናይሮቢ፣ አልጀርስ፣ ዋሸንግተን ዲሲ፣ ለንደን እና ጣልያን ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስከበር የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ ስራዎች ማከናወናቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል።