ዩኤኢ በግድቡ ዙሪያ የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ የድርድር ጥረቶች እንዲቀጥሉ ጥሪ አቀረበች
የሶስቱን ሀገራት መብት እና የውሃ ደህንነት ሁሉም እንደሚቀበልም ነው የዩኤኢ ያስታወቀችው
ዩኤኢ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶቹ እና ድርድሮቹ ገንቢ እና ፍሬያማ ሆነው እንዲቀጥሉ ያላትን ጽኑ ፍላጎትም ገልጻለች
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶችን በውይይትና ዲፕሎማሲያዊ የድርድር መንገዶች ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (ዩኤኢ) አስታወቀች፡፡
ዩኤኢ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ ላይ ያሏቸውን ልዩነቶች “ገንቢ በሆኑ ዲፕሎማሲያዊ የውይይት እና ፍሬያማ የድርድር መንገዶች ለመፍታት የጀመሯቸውን ጥረቶች አጠናክረው እንዲቀጥሉ” ያላትን ጽኑ ፍላጎትም በውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ ጥሪ አቅርባለች፡፡
ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ “በዓለም አቀፍ ህግጋት እና መርሆዎች መሰረት መስራቱ መፍትሔ ላይ ለመድረስ ይበጃል” ብሏል፡፡
ይህን ጨምሮ ደህንታቸውን፣ መረጋጋትና ዘላቂ ልማታቸውን በሚያሳካ እና የቀጣናውን ሃገራት የጋራ ብልጽግናና ትብብር ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ የሶስቱን ሀገራት መብትና የውሃ ደህንነት ሁሉም እንደሚቀበልም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ትናንት “ከግብጽ የውሃ ድርሻ ላይ ማንም አንዲትንም ጠብታ ሊነካ አይችልም”ሲሉ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡
ማሳሰቢያውን ተከትሎ ሳዑዲን ጨምሮ 4 የተለያዩ የአረብ ሃገራት በግድቡ ጉዳይ ግብጽን ደግፈው መግለጫ ማውጣታቸውም አይዘነጋም፡፡