ግብፅ እና ኢትዮጵያ ሃሙስ የማጣሪያ ጨዋታ ያደርጋሉ
የግብፅ ብሔራዊ ቡድን እና የሊቨርፑል አጥቂ መሐመድ ሳላህ ሀገሩ ሰኔ ሁለት ቀን 2014 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምታደርገው ጨዋታ እንደማይሰለፍ የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
የግብፅ ብሔራዊ ቡድን በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን ሐሙስ ከኢትዮጵያ ጋር በማላዊ የሚያከናውነው ካለ አጥቂው ሞ ሳላህ መሆኑን የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
ዕሁድ ዕለት ግብፅ ከጊኒ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ላይ ከነጉዳቱ የተሰለፈው ሳላህ ኢትዮጵያን ከሚገጥመው ስብስብ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
"ግብጾች ወጪ ችለን ካይሮ ተጫወቱ ቢሉንም የክብር ጉዳይ በመሆኑ ውድቅ አድርገነዋል" - የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ትናንትና በማላዊ ባደረገው ጨዋታ ሁለት ለአንድ ተሸንፏል፡፡ የማላዊ ብሔራዊ ቡድንም ሆነ የኢትዮጵያ አቻው ያስቆጠሯቸው ግቦች በፍጹም ቅጣት ምት የተገኙ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከግብፅ ጋር የሚጫወተው ማላዊን በገጠመበት በማላዊ ሊሎንግዌ ቢንጉ ብሔራዊ ስቴዲየም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን በሜዳው ማድረግ ያለበትን ጨዋታ ከሀገር ውጭ ለማድረግ ተገደደው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ደረጃውን የጠበቀ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደሌለ ከገመገመ በኋላ ነው፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ጋር የጨዋታ መርሃ ግብር ያላት ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በካይሮ ለመጫወት ጥያቄ አቅርባ እንደነበር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መግለጹ ይታወሳል፡፡