የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን በተመለከተ የሚጠበቀው የካፍ ውሳኔ ዛሬ ወይ ነገ ይታወቃል ተባለ
ካፍ ኢትዮጵያ በሜዳዋ የምታደርጋቸው ጨዋታዎችን በገለልተኛ ሀገር እንድታከናውን መወሰኑ ይታወሳል
ካፍ ስታዲየሙን በተመለከተ ተስፋ ሰጪ ግምገማ ማድረጉ ተገልጿል
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን በተመለከተ ያደረገውን የግምገማ ውሳኔ ዛሬ ወይ ነገ ያሳውቃል ተባለ፡፡
ውሳኔው ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ ይችል ወይስ አይችልም ስለሚለው የሚታወቅበት ነው፡፡
ለዚህም በጥቅምት ወር ባሳለፈው ውሳኔ ያስቀመጣቸው መስፈርቶች እስኪሟሉ ድረስ ኢትዮጵያ በሜዳዋ የምታደርጋቸው ጨዋታዎችን በገለልተኛ ሀገር እንድታከናውን ወስኖ የነበረው ካፍ ትናንት ሃሙስ ገምጋሚ ልኮ የስታዲየሙን አሁናዊ ይዞታ ገምግሟል፡፡
ግምገማው ስታዲየሙ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ዝቅተኛ መስፈርቶች አሟልቷል ወይ የሚለውን ለማረጋገጥ ነው ያሉት የአማራ ክልል ቢሮ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ዋና ዳይሬክተር አቶ ባንተ አምላክ ሙላት ስታዲየሙ ጨዋታዎችን ያጣውን ፈቃድ መልሶ ለማግኘት የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ ግብረ ምላሾች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
ከአሁን ቀደም በካፍ የተጠየቁት መስፈርቶች ጥቃቅን እንደነበሩ በማስታወስም ይሟሉ የተባሉ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የተጫዋቾች መተላለፊያዎች (ተነል) ከጣሊያን መጥቶ ተገጥሟል፣ አራት የመልበሻ ክፍሎች በአዲስ መልክ ተዘጋጅተዋል፣ ሁለት የልምምድ ሜዳዎችን ጨምሮ የዋናው ሜዳ ሳር ተስተካክሏል፣ እንግዶች የሚስተናገዱባቸው ካፌዎች እና ሌሎች በካፍ ነጥብ የሚያሰጡ የመብራት፣ የካሜራ እና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች በራሱ በክልሉ ዐቅም እንዲሟሉ መደረጉንም ነው አቶ ባንተ አምላክ የተናገሩት፡፡
በጦርነት ምክንያት ለከፋ ችግር የተጋለጠው ክልሉ ብሔራዊ ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ከሚጫወት በሚል የተቻለውን ድጋፍ ማድረጉንም አስቀምጠዋል፡፡
ካፍ የአፍሪካ ሀገራት የ2022 የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ጊዜን አራዘመ
የስታዲየሙን ሁኔታ በማሻሻል ውድድር የማስተናገድ ፈቃዱን መልሶ እንዲያገኝ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየቱን የገለጸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በመጫወቻ ሜዳ፣ በሚዲያ ክፍል፣ በቪአይፒ ፣ በተመልካች ፋሲሊቲ፣ በህክምና ክፍል እና ተያያዥ ግብዓቶች ላይ የተደረገውን የማሻሻያ ሥራ ከካፍ ተወክለው የመጡት ሚስተር ኢቫን ኪንቱ በስታዲየሙ ተገኝተው መመልከታቸውን አስታውቋል።
በመሆኑም የስታዲየሙን ይዞታ በመልካም ጎኑ የገመገሙት የካፍ ተወካይዎች ግምገማቸውን የተመለከተ ሪፖርት መላካቸውንና ውሳኔው ምናልባትም ዛሬ ወይ ነገ ሊታወቅ እንደሚችልም ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ባንተአምላክ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የካፍን ፈቃድ የምታገኝ ከሆነ ከግብፅ ጋር የምታደርገውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ ጨዋታን ጨምሮ ያሉባትን ሌሎች ሶስት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች በሜዳዋ ታደርጋለች፡፡
ዋሊያዎቹ ከፈርዖኖቹ ጋር በመጪው ግንቦት መጨረሻ ላይ እንደሚጫወቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡
አዎንታዊ ሊሆን እንደሚችል የተጠበቀው የካፍ ውሳኔ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሊኖረው የሚችለው አበርክቶ ካለ በሚል አል ዐይን አማርኛ የጠየቃቸው የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ "በጣም ትልቅ አድቫንቴጅ አለው" ብለዋል ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው በደጋፊው ፊት ከተጫወተ ሁለት ዓመት እንዳለፈው በመጠቆም፡፡
"መጀመሪያ በኮቪድ ምክንያት ከአይቮሪኮስት ጨዋታ በኋላ ጨዋታዎችን ካለ ደጋፊ በዝግ ስታዲየም ስናደርግ ነበር መጨረሻ ደግሞ በእገዳው ምክንያት ከጋና ጋር ከሃገር ውጭ (በደቡብ አፍሪካ) ተጫውተናል፤ በዚህ በሃገር መጫወት የሚያገኘውን አድቫንቴጅ እና ከደጋፊው እናገኝ የነበረውን ድጋፍ አጥተናል" ነው አሰልጣኝ ውበቱ ያሉት፡፡
"የሚሳካ ከሆነ በሜዳችን የምናደርጋቸውን ሶስት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች በደጋፊዎቻችን ፊት በህዝባችን ታጅበን በጥሩ ሞራል ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንጫወታለን ይረዳናልም ማለት ነው" ሲሉም ስለሚኖረው ጥቅም ገልጸዋል፡፡