ካፍ የባህር ዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማካሄድ ብቁ አይደለም አለ
ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ያለባትን የማጣያ ጨዋታ የምታካሂድበትን ሜዳ በ2 ቀናት ውስጥ እንድታሳውቅ ካፍ አሳስቧል
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በካፍ ውሳኔ በውሳኔው መበሳጨታቸውን ተናግረዋል
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የባህር ዳር ስታዲየምን በተመለከተ ያደረገውን የግምገማ ይፋ አድርጓል።
ውሳኔውን በተመለከት ካፍ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው ደብዳቤ፤ ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደማይችል አስታውቋል።
ካፍ ያስቀመጣቸው መስፈርቶች እስኪሟሉ ድረስ ኢትዮጵያ በባህር ዳር ስታዲየም የአፍሪካ ዋንጫ የምጣሪያ ጨዋታዎችን ማካሄድ እንደማትችል በደብዳቤው አሳውቋል።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ከግብጽ ጋር ያለባትን ጨዋታ የምታካሂድበትን በካፍ ማረጋገጫ ያገኘ ስታዲየም በቀጣይ ሁለት ቀናት ውስጥ እንድታሳውቅም ካፍ አሳስቧል።
ኢትዮጵያ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ስታዲየም መርጣ የማታሳውቅ ከሆነ የጨዋታው ስፍራ በተቃራኒ ተጋጣሚ (ግብፅ) ሜዳ እንደሚደረግም ካፍ በደብዳብው አሳውቋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በካፍ ውሳኔ በውሳኔው መበሳጨታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ስለ ውሳኔው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ጭምር ደውለው ማብራያ መጠየቃቸውን የገለጹት አቶ ኢሳያስ፤ “ሆኖም በውሳኔው ከማዘን ውጭ ያገኙት አዎንታዊ ምላሽ የለም” ብለዋል።
ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ዝቅተኛ መስፈርቶችን አላሟላም በሚል ከወራት በፊት የተላለፈውን እገዳና የተሰጠውን ምክረ ሐሳብ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሜዳውን የሳር ይዞታ የማሻሻልና የተጫዋቾች መተላለፊያ ተኔል እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ ተደርጎ መጥቶ በነበረው ገምጋሚ ቡድን መልካም ምላሽ አግኝቶ እንደነበረ የገለፁት አቶ ኢሳያስ፤ ውሳኔው ሃገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ሳያስገባ የተላለፈ መሆኑን ተናግረዋል።
ውሳኔውን ተከትሎ ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ደብዳቤ መጻፋቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጭ ልትጫወት የምትችልበትን ሜዳ በፈረንጆቹ እስከ ግንቦት 12 ድረስ እንድታሳውቅ ካልሆነ በተጋጣሚዋ ሜዳ ለመጫወት እንደምትገደድ ካፍ አስታውቋል።
ስለዚህ ጉዳይ የጠየቅናቸው አቶ ኢሳያስ፤ የምንጫወትበትን ሜዳ ለማዘጋጀት እየሰራን ነው የደረስንበትን እናሳውቃለን ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ተወካዮች በሳለፍነው ሳምንት ሀሙስ ባለሙያዎችን በመላክ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ላይ ግምገማ ማካሄዱ ይታወሳል።
ግምገማው ስታዲየሙ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ዝቅተኛ መስፈርቶች አሟልቷል ወይ የሚለውን ለማረጋገጥ ነው እንደነበረም የአማራ ክልል ቢሮ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ዋና ዳይሬክተር አቶ ባንተ አምላክ ሙላት መናገራቸው ይታወሳል።
ከአሁን ቀደም በካፍ የተጠየቁት መስፈርቶች ጥቃቅን እንደነበሩ በማስታወስም ይሟሉ የተባሉ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ መደረጉን ገልጸው ነበር።
የተጫዋቾች መተላለፊያዎች (ተነል) ከጣሊያን መጥቶ ተገጥሟል፣ አራት የመልበሻ ክፍሎች በአዲስ መልክ ተዘጋጅተዋል፣ ሁለት የልምምድ ሜዳዎችን ጨምሮ የዋናው ሜዳ ሳር ተስተካክሏል፣ እንግዶች የሚስተናገዱባቸው ካፌዎች እና ሌሎች በካፍ ነጥብ የሚያሰጡ የመብራት፣ የካሜራ እና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች በራሱ በክልሉ ዐቅም እንዲሟሉ መደረጉንም ነበር አቶ ባንተ አምላክ የተናገሩት።
ዋሊያዎቹ ከፈርዖኖቹ ጋር በመጪው ግንቦት መጨረሻ ላይ እንደሚጫወቱ መገለጹ ይታወሳል።