በአዲስ አበባ የኮሮና መከላከያ መመርያዎችን በተላለፉ ከ1 ሺህ በላይ ተሸከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ
የኮቪድ 19 መከላከያ ተግባራት አለማከናወን እስከ 2 ሺ ብር ያስቀጣል
በአዲስ አበባ ከኮሮና ጋር በተያያዘ በተሸከርካሪዎች ላይ በተወሰደ እርምጃ ከ4.6 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ በተላለፉ 1,002 ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡
ቢሮው ከከግንቦት 2 እስከ 10/2013 ዓ.ም ብቻ ትርፍ በመጫን 603፣ ማስክ ባለማድረግ 204፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል 91፣ መስመር ባለመሸፈን 65፣ ታፔላ ባለመስቀል 38 እና በስራ ሰዓት መቆም 1 በድምሩ 1002 ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ወስጃለሁ ብሏል፡፡
በሚያዝያና መጋቢት ወር 10 ሺህ 305 ተሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ከ 4 ሚሊዮን 609 ሺህ ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉም ነው ቢሮው ያስታወቀው፡፡
ትርፍ መጫን፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ የኮቪድ 19 መከላከያ ተግባራት አለማከናወን፣ በስራ ሰዓት ያለ ሥራ ቆሞ መገኘት እና ታፔላ ሳይሰቅል መስራት ከ5 መቶ እስከ 2 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በመመሪያው ተደንግጓል፡፡ ከባድ ተሽከርካሪዎች የተፈቀደላቸውን ሰዓት ሳያከብሩ ከተገኙ 5 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣም እንዲሁ፡፡
መመሪያው ከወጣበት ከሚያዝያ 26/2013 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የንቅናቄ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት በዋና ዋና ተርሚናሎች እና መስመሮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ካሉ አጠቃላይ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 62 በመቶ ያህሉ በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ከፌደራል ትራንስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።