በሶማሌ ክልል በዘጠኝ ዞኖች የተከሰተው ድርቅ ዜጎችን እያፈናቀለ ነው ተብሏል
ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር ንግግር ተጀምሯልም ተብሏል
በክልሉ በድርቁ ምክንያት ዕርዳታ የሚሹ ዜጎች ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ መድረሱን የክል መንግስት አስታውቋል
በሶማሌ ክልል ከሚገኙት 11 ዞኖች ውስጥ በዘጠኙ ድርቅ መከሰቱን የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ድርቅ የተከሰተው በመኸር እና በበልግ ወቅቶች ዝናብ ማግኘት የነበረባቸው ዘጠን ዞኖች በቂ ዝናብ ባለማግኘታቸው እንደሆነ ክልሉ ገልጿል።
በሱማሌ ክልል ከፋፋን እና ሲቲ ዞኖች ውጭ ያሉት ዘጠኙ ዞኖች ዝናብ የሚያገኙት ከቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል በተለያየ መልኩ በመኸርና በበልግ ወራት ቢሆንም ባለፈው በልግ እና በአሁኑ መኸር በቂ ዝናብ በክልሉ ድርቅ መከሰቱን የአደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ ይፋ አድርጓል።
ዘጠኙ ዞኖች በ2013 ዓ.ም በነበረው የበልግ ወቅት ያገኙት ዝናብ ዝቅተኛ በመሆኑ እንዲሁም ሊጠናቀቅ ቀናት የቀሩት መኸር የተጠበቀው ዝናብ ባለመዝነቡ ላለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ድርቅ ተከስቷል።
አሁን ላይ ይጠበቅ የነበረው የመኸር ዝናብ ባለመዝነቡ ድርቁ ሊቀጥል እንደሚችል ስጋት እንዳለ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ረዘም ላለ ጊዜ የሆነው የበጋ ወቅት እየገባ በመሆኑ ድርቁ ይቀጥላል የሚል ሥጋት እንዳለ የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ በሽር ዓረብ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
አል ዐይን አማርኛ ከክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ ባገኘው መረጃ መሰረት በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በ 78 ወረዳዎች ላይ የውኃ እጥረት ተከስቷል። ከዚህ ባለፈም ድርቁ በ 49 ወረዳዎች የእንስሳት ግጦሽ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል ነው የተባለው።
በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት እስካሁን 146 ሺ 806 እንስሳት መሞታቸውን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪው አቶ በሽር ዓረብ ለአል ዐይን ተናግረዋል።
ከእንስሳት ሞት ባለፈም በክልሉ በድርቁ ምክንያት ዕርዳታ የሚሹ ዜጎች ከ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ እንደሆነም ነው የተጠቀሰው።
ድርቁን መቋቋም ያቃታቸውና አቅም ያላቸው ነዋሪዎች እንስሳቶቻቸውን በመኪና እየጫኑ ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ በመጓጓዝ ወደ ክልሉ ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ አቅራቢያ እየመጡ መሆኑንም ቡድን መሪው ጠቅሰዋል።
የክልሉ መንግስት የድርቁን አደጋ ለመቋቋም ከአንድ ወር በፊት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ማፅደቁን የገለጹት ቡድን መሪው ይህ ገንዘብ በቂ እንደማይሆንም ተናግረዋል።
የፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እስካሁን ድጋፍ ማድረግ እንዳልጀመረ የተናገሩት አቶ በሽር በክልሉ እና በፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መካከል የመረጃ ልውውጥ እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ድርቁን ለመቋቋም የሚያስችል ድጋፍ ለማግኘት ለረጅ አካላትና ለተቋማት የተጠናቀረ ሰንድ ተዘጋጅቶ እንደተላከም ነው ቡድን መሪው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የ50 ሚሊየን ብር የአይነት ድጋፍ እንደሚየደረግ መገለጹ ይታወሳል።