የሞሮኮን የድል ጉዞ ለመደገፍ የተጫዋቾች እናቶች ስታዲየም ተገኝተዋል
ሞሮኮ ሲያሸንፉ አሽራፍ ሃኪሚ ጎል እንዳስቆጠረ ተንደርድሮ ሄዶ እናቱ አቅፎ ስሟል
ዛሬም ስፔንን በጥሎ ማለፉ ሲገጥሙ ይሄው በስታዲየም የሚመለከተው የእናቱና የደጋፊዎቹ የሞራል ድጋፍ ይጠበቃል
ሞሮኮ በኳታሩ የአለም ዋንጫ አስደናቂ ቆይታን እያሳለፈች ነው።
በኳታር የሚኖሩ ከ15 ሺህ በላይ የሞሮኮ ዜጎች በሜዳቸው የሚጫወቱ ያህል ስታዲየሞችን ሲያደምቁ ተስተውሏል።
ከደጋፊው ባሻገር የተጫዋቾቹ ቤተሰቦች በስታዲየም መገኘት ሌላ ድባብና የድል ብርታት ፈጥሯል ነው የተባለው።
የአትላስ አንበሶቹ ቤልጂየምን 2 ለ 0 ሲያሸንፉ አሽራፍ ሃኪሚ ጎል እንዳስቆጠረ ተንደርድሮ ሄዶ የሳመው እናቱን ነው።
የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንት ጀርመኑ አጥቂ ጨዋታው እንደተጠናቀቀም በርካቶች የተቀባበሉትን ምስል “እናቴ እወድሻለሁ” ከሚል ጽሁፍ ጋር ኢንስታግራም ላይ አጋርቷል።
የሃኪሚ እናት ብቻ አይደሉም ወደ ዶሃ ያቀኑት፤ የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን አባላት የአለም ዋንጫውን እንዲታደሙ የመረጧቸው ቤተሰቦቻቸውም ኳታርን አድምቀዋታል።
የአትላስ አንበሶቹ ያረፉበት በዶሃ የሚገኘው ዌስት ቤይ ሆቴል እና ዙሪያውም የሞሮኳውያን ግዛት መስሏል ነው የተባለው።
ሞሮኮ የምድብ ጨዋታዎቿን ስታደርግ በስታዲየም የነበሩት የቡድኑ አባላት ቤተሰቦች በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን ይታዩ ነበር።
ዛሬም ስፔንን ሲገጥሙ ኢጁኬሽን ሲቲ ስታዲየም በቀያይ ሰንደቆች ይደምቃል፤ የነሃኪሚ እናቶችም የልጆቻቸውን ሞራል ከፍ ለማድረግ “አይዞህ ልጄ” ይላሉ።
ሞሮኮ፤ ቤልጂየም እና ካናዳን አሸንፋ ከክሮሽያ አቻ ተለያይታ በ7 ነጥብ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።
ይህን ያሳካው ቡድን አባላት ሞሮኮ በ1986 በአለም ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ 16 ውስጥ ስትገባ አልተወለዱም።
በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ከ20 በላይ ተጫዋቾችን የያዘው ስብስብ አዲስ ታሪክ ለማጻፍ ዛሬ 12 ስአት ላይ ስፔንን ይገጥማል።
በ2010ሩ የደቡብ አፍሪካ የአለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ ደርሳ ዋንጫውን ያንሳችው ስፔን የአፍሪካዊቷን ሀገር ጥላ ሩብ ፍጻሜውን እንደምተቀላቀል ሰፊ ግምት ተስጥቷታል።
ስፔን በአለም የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ 7ኛ ላይ ብትቀመጥም 22ኛ ላይ ያለችው ሞሮኮ እንደምታሸንፍ ነው የአትላስ አንበሶቹ ደጋፊዎች የሚያምኑት።
ሞሮኮ ምንም ሳትሸነፍ ከምድቧ በ7 ነጥብ በአንደኝነት አጠናቃለች፤ በአንጻሩ ስፔን በ4 ነጥብ ጀርመንን በጎል ክፍያ በመብለጥ ነው ጃፓንን ተከትላ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለችው።
ሞሮኮ እና ስፔን ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱን ስፔን አሸንፋለች፤ በሩስያው የ2018 የአለም ዋንጫ ደግሞ 2 ለ 2 ተለያይተዋል።
የዛሬው ፍልሚያ አሸናፊ ምሽት 4 ስአት ከሚጫወቱት ፖርቹጋልና ስዊዘርላንድ አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ይገናኛል።