ሞሮኮ እና ጀርመን ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል ይጫወታሉ
አፍሪካዊቷ ሞሮኮ ከካናዳ ጋር 12 ስአት፤ ጅርመን ደግሞ ከኮስታሪካ ምሽት 4 ስአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ
በተለይ ጃፓንን ከስፔን የሚያገናኘው ጨዋታ ለጀርመንም ወሳኝ በመሆኑ ይጠበቃል
የአለም ዋንጫው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ ሞሮኮ እና ጀርመን ተጠባቂ ጨዋታ ያደርጋሉ።
12 ስአት ላይ ሞሮኮ ከካናዳ፤ ቤልጂየም ከክሮሽያ ይጫወታሉ።
አል ቱማማ ስታዲየም ላይ መውደቋን ካረጋገጠችው ካናዳ ጋር የምትፋለመው ሞሮኮ ማሸነፍ አልያም አቻ እና የክሮሽያ መሸነፍ ለጥሎ ማለፉ ያበቃታል።
ከምድቡ ከክሮሺያ ጋር በእኩል 4 ነጥብ በጎል ክፍያ ተበልጣ ሁለተኛ ላይ የተቀመጠችው ሞሮኮ፥ ቤልጂየም በሰፊ ጎል ልዩነት ክሮሽያን ካሸነፈችም ድል ማድረግ ሳይጠበቅባት ወድ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድል አላት።
ምሽት 4 ስአት ላይ ደግሞ የምድብ 5 ተጠባቂ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
የአራት ጊዜ የአለም ዋንጫ ሻምፒዬኗ ጀርመን ኮስታሪካን ትገጥማለች፤ ምድቡን በአራት ነጥብ የምትመራው ስፔንም ከጃፓን ጋር ትጫወታለች።
በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ የያዘችው ጀርመን ወደ ጥሎ ማለፉ ለመግባት ማሸነፍ አይበቃትም፤ የስፔንን በብዙ ጎል መሸነፍ ትጠብቃለች። ጃፓን እና ኮስታሪካ ግን በማሸነፍ ብቻ ቀጣዩን ዙር መቀላቀል ይችላሉ።
በ20 የአለም ዋንጫዎች የተሳተፈው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ከብራዚል በመቀጠል ረጅም የተሳትፎ ታሪክ አለው።
ከ1938ቱ እና 2018 የአለም ዋንጫ ውጭ በ17ቱም የአለም ዋንጫዎች ከሩብ ፍፃሜ የተሻገረ ውጤት አስመዝግበዋል።
የዛሬው ፍልሚያስ በታሪካቸው ሶስተኛው መጥፎ አጨራረስ ይሆናል ወይስ ድል እና እድል ይቀናቸዋል? አል ባይት ስታዲየም ምሽት 4 ስአት ላይ ተጠባቂውን ፍልሚያ ያስተናግዳል።