በዩክሬን የሚደረግ ማንኛውም አይነት የኔቶ ወታደራዊ ስምሪት መዘዙ እንደሚከፋ ሩሲያ አስጠነቀቀች
በአዋሳኝ ድንበሮች የሚደረግ የሩሲያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስጋት እንደፈጠረባት ዩክሬን አስታውቃለች
አሜሪካ “ሩሲያ በምስራቃዊው የዩክሬን ክፍል እየፈፀመች ያለው ትንኮሳ ያሳስበኛል” ብላለች
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት/NATO/ በትናንትናው እለት ፣ ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ድንበር አቅራቢያ የምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያሳስበውና ይህም ወደ ግጭት አድጎ የዩክሬን ዳንባስ ግዛትን ለጥፋት እስከመዳረግ ሊደርስ እንደሚችል ያለውን ስጋት ገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም የሩሲያ መንግስት ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ “በድንበር አቅራቢያ የማደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ራስን ለመከላከል የሚደረግ እንጂ ማንንም ሊያሰጋ አይገባም” ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዩክሬን መንግስትና አፍቃሬ-ሩሲያ ብለው በሚጠሯቸው ኃይሎች መካከል ያለው ፍጥጫ ግን በቀላሉ የማይታይና “ትንኮሳዎች” ጭምር የሚታዩበት እንደሆነም ነው የሩስያው ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ የተናገሩት፡፡
የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ፣ ከዩክሬኑ አቻቸው አንድሪ ታራን ባደረጉት ውይት “በአሁኑ ጊዜ ሩሲያ በምስራቃዊ የዩክሬን ክፍል እየፈፀመችች ያለው ትንኮሳ ያሳስበኛል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ይህ የአሜሪካ አስተያየት ያልተመቻት የምትመስለው ሩሲያ ፣ በኔቶ / NATO/ አማካኝነት በዩክሬን የሚደረግ ማንኛውም ወታደራዊ ስምሪት የሩሲያ-ዩክሬን ድንበር ውጥረትን የሚያባብስ ከመሆኑም በላይ “ሞስኮ ለደህንነቷ ስትል ተጨማሪ እርምጃ እንድትወስድ የሚያስገድዳት ነው ፤ በመሆኑም እንዳይታሰብ” ስትል አስጠንቅቃለች፡፡ ምዕራባውያኑ ምንም አይነት ኃይል ወደ ዩክሬን ከላኩ ሩሲያ እርምጃ እንደምትወስድ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
የዩክሬኑ ወታደራዊ አዛዥ ሩስላን ሆምቻክ ፣ ሰሞኑን ሩሲያ ከዩክሬን በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ ወታደራዊ ይዞታዎችን እያጠናከረች ነው ሲሉ በትናንትናው ዕለት ክስ አቅርበው ነበር፡፡
አፍቃሬ- ሩሲያውያን ስልታዊ በሆነ መንገድ ከአሁን ቀደም ያደረግነውን የተኩስ አቁም ስምምነት እየጣሱ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እንደ አዱስ የተቀሰቀሰው የሩሲያ እና የዩክሬን የድንበር ውዝግብ ዳግም ያየለ ሲሆን ፣ ዩክሬን ከአፍቃሬ ሩሲያውያን ተገንጣይ ኃይሎች ጋር ወደ ጦርነት ልትገባ እንደምትችል እና ይህም የውጭ ኃይሎችን ሊጋብዝ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡