ሰሜን ኮሪያ እስከ 10ኛ ባለው ደረጃ ውስጥ አልተካተተችም
አለማችን በየጊዜው የደህንነት ስጋቷ እየጨመረ መሄዱ ሀገራት ወታደራዊ አቅማቸውን ማፈርጠም ላይ እንዲበረቱ አድርጓቸዋል።
በየአመቱ የሀገራትን ወታደራዊ አቅም ደረጃ የሚያወጣው "ግሎባል ፋየርፓወር" የ2023 የሀገራትን ደረጃ አውጥቷል።
የወታደሮችና ጦር መሳሪያዎች ብዛት፣ አመታዊ የጦር በጀት እና የጦር መሳሪያ ልማትን መሰረት አድርጎ የሚወጣው ደረጃ ሰሜን ኮሪያን እሰከ10ኛ ባለው ደረጃ ውስጥ አላካተተተም።
"ግሎባል ፋየርፖወር" የ2023ን የጠንካራ ወታደራዊ ሃይል ባለቤት ሀገራት ደረጃ እንደሚከተለው አውጥቷል፦
1. አሜሪካ
በበርካታ መመዘኛዎች ቀዳሚነቱን የያዘችው አሜሪካ ከ13 ሺህ 300 በላይ የጦር አውሮፕላኖች፤ 983 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች አሏት። ከ100 በላይ የጦር መርከቦቿም ወታደራዊ ተፅዕኖዋን አጎልብቶላታል ይላል ግሎባል ፋየር ፓወር።
አሜሪካ በ2023 የያዘችው የ730 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ በጀትም ሶስተኛ ደረጃን ከያዘችው ቻይና በሶስት እጥፍ የሚልቅ ነው።
2. ሩሲያ
በዩክሬን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ጀምሬያለው ካለች ሁለተኛ አመቷን ልትይዝ የተቃረበችው ሩሲያ ፈርጣማ ወታደራዊ ሀይል በመገንባት ከአሜሪካ ቀጥላ ተቀምጣለች።
ከ4 ሺህ 100 በላይ የጦር አውሮፕላኖች ባለቤት የሆነችው ሞስኮ ከጥቃት የሚያመልጡ የጦር አውሮፕላኖች እና መርከቦች እንዳሏል የግሎባል ፋየርፓወር ሪፓርት ያሳያል። ግዙፉ የሩሲያ መገዳደሪያ ግን የኒዩክሌር ጦር መሳራያ መሆኑንም በማከል።
3. ቻይና
ባለፉት አስርት አመታት ዋሽንግተንን በምጣኔ ሀብት ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ ቁመና መፎካከር የጀመረችው ቤጂንግ በዚህ ፍጥነት ከቀጠለች ቀዳሚዋ ሀገር እንደምትሆን ይጠበቃል።
ቻይና በራሷ አቅም የምድር፣ የአየር እና የባህር ሃይሏን አቅም ለማሳደግ፤ መርከቦች እና አውሮፕላኖች ለመስራት የምታደርገው ጥረትም ከሰው ሀይልእድሏ ጋር ተዳምሮ ቀጣዩዋ መሪ ትሆናለች የሚለውን ግምት አሰጥቷታል።
ከ2 ሚሊየን በላይ ወታደሮች ያሏት ቤጂንግ፣ የ3 ሺህ 285 የጦር አውሮፕላኖችና 78 ባህርሰርጓጅ መርከቦች ባለቤት ናት።
4. ህንድ
የህንድ ወታደራዊ አቅም ከህዝብ ብዛቷ ጋር የሚያያዝ ነው። በህዝብ ብዛት ከቻይና መሪነቱን የተቀበለችው ኒውደልሂ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ወታደሮች አሏት።
ከ653 ሚሊየን በላይ ዜጋዋም ወታደራዊ ሃይሉን መቀላቀል የሚችል ነው ተብሏል።
ህንድ ከ2 ሺህ በላይ የውጊያ አውሮፕላኖችና 150 የጦር መርከቦች እንዳሏት ተጠቅሷል።
5. ብሪታንያ
አውሮፓዊቷን ሀገር አምስተኛ ደረጃ ያስቀመጣት ጠንካራ የባህርና አየር ሀይል መገንባቷ እና የምትይዘው አመታዊ በጀት ነው።
ሀገሪቱ በአለም ላይ ከአንድ በላይ አውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ መርከቦች ካሏቸው ጥቂት ሀገራት አንዷ ናት።
ሁለት አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ያላት ብሪታንያ፥ ከ70 በላይ የጦር መርከቦች እና ኒዩክሌር የሚታጠቁ ባህር ሰርጓጂ መርከቦች ባለቤት መሆኗን የግሎባል ፋየርፓወር ሪፓርት ያሳያል።
6. ደቡብ ኮሪያ
ከጎረቤቷ ሊቃጣ ለሚችል ጥቃት ዝግጁነቷን እያጠናከረች የምትገኘው ደቡብ ኮሪያ በከለማችን ስድስተኛው ጠንካራ ጦር ገንብታለች ተብሏል።
ሴኡል ከ720 በላይ የጦር አውሮፕላኖችና 739 ሄሊኮፕተሮች ባለቤት ስትሆን ከ133 ሺህ በላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አሏት።
7. ፓኪስታን
ፓኪስታን ከባለፈው አመት ሁለት ደረጃዎችን አሻሽላ ሰባተኛ ደረጃን ይዛለች።
ከ1 ሺህ 400 በላይ የጦር አውሮፕላኖች ያሏት ኢስላማባድ፥ የታንኮቿን ብዛት ከ3 ሺህ 700 በላይ አድርሳለች። የወታደሮቿ ቁጥርም ወደ 654 ሺህ ከፍ ማለቱ ተገልጿል።
8. ጃፓን
የሩቅ ምስራቋ ጃፓን 1 ሺህ 400 የጦር አውሮፕላኖች ያለው ጠንካራ ጦር ባለቤት ናት። ከ111 ሺህ በላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎቿ እና ሌሎች መመዘኛዎችም ጠንካራ ጦር ካላቸው ሀገራት አስመድቧታል።
9. ፈረንሳይ
ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጦሯን ለማስወጣት የተገደደችው ፓሪስ ከ700 በላይ የጦር አውሮፕላኖች እና ከ100 የጦር መርከቦች አሏት።
10. ጣሊያን
404 ሄሊኮፕተሮች እና ሁለት አውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ መርከብ ባለቤቷ ጣሊያን 10ኛ ደረጃን ይዛለች።
1 ሺህ 65 የጦር አውሮፕላኖች ያላት ቱርክ ጣሊያንን ተከተላ 11ኛ ላይ ስትቀመጥ 35 የውጊያ አውሮፕላኖችና ከ4 ሺህ በላይ ታንኮች ያላት ኢራን 17ኛ ደረጃን ይዛለች።