ቻይና በኒዩክሌር የጦር መሳሪያዎች ላይ በስፋት እየሰራች መሆኑ ተገልጿል
የአለም ሀገራት የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ የሚያደርጉት ፉክክር እየጨመረ መሄዱ ተነግሯል።
እስከ ጥር 2023 ድረስም ዘጠኙ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ሀገራት (እስራኤል በይፋ ባትገልጽም) 12 ሺህ 512 የኒዩክሌር አረር እንዳላቸው የስቶኮልም አለማቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም መረጃ ያሳያል።
ከዚህ ውስጥ 9 ሺህ 576ቱ በተፈለገው ስአት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ ብሏል ተቋሙ።
በሚሳኤሎች እና የጦር አውሮፕላኖች ላይ ተጠምደው የሚጠባበቁ የኒዩክሌር አረሮች ቁጥርም 3 ሺህ 844 መሆኑን ጥናቱ ያሳያል።
ሀገራት እስከ ጥር 2023 ያላቸው የኒዩክሌር አረር ብዛት ከባለፈው አመት በ86 ብልጫ ያለው ነው፤ ከዚህም ውስጥ ቻይና (60)፣ ሩሲያ (12)፣ ፓኪስታን (5)፣ ሰሜን ኮሪያ (5) እንዲሁም ህንድ (4) ድርሻ አላቸው ተብሏል።
በጸጥታው ምክርቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው አምስቱ ሀገራት በ2021 “በኒዩክሌር ጦርነት ማንም አሸናፊ አይሆንም” ቢሊም የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎቻቸውን ቁጥር በመጨመር ላይ ተጠምደዋል።