የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረትም በ2024 ከፍተኛው ጣሪያ ላይ ደርሶ ነበር
በዛሬው እለት የሚጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 አመት የምርጫ አመት ነበር።
4 ቢሊየን የሚጠጋ ህዝብ ያላቸው ከ70 በላይ ሀገራት ምርጫ አካሂደው አዳዲስ መሪዎች ወደ ስልጣን የመጡበት አመት ሆኗል።
ከሩዋንዳ እስከ ህንድ፤ ከአሜሪካ እስከ ሩሲያ፣ ከኢራን እስከ ደቡብ አፍሪካ የተደረጉት ምርጫዎች የአለማችን የቀጣይ አመታት እጣ ፈንታ የሚወስኑ ነበሩ።
በህዝብ ብዛት ቀዳሚ የሆኑት ህንድ፣ አሜሪካ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ፓኪስታን እና ባንግላዴሽ በዚሁ አመት ምርጫ ማካሄዳቸው የሚታወስ ነው።
ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ የአለማችን ህዝብ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት መሪዎቹን መርጧል።
ፑቲን እስከ 2030
ሩሲያ በመጋቢት ወር 2024 ያደረገችው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቭላድሚር ፑቲንን ለድጋሚ ድል አብቅቷል።
ሩሲያን ለ25 አመት የመሩት ፑቲን ለተጨማሪ ስድስት አመት በክሬምሊን እንዲቆዩ ያደረገው ምርጫ የቀድሞው የኬጂቢ ሰላይ ሩሲያን ለረጅም ዓመታት በመምራት የሚታወቁትን ጆሴፍ ስታሊን ክብረ ወሰን በእጃቸው እንዲያስገቡ የሚያስችላቸው ሆኗል።
ተፎካካሪ አልባ በነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፑቲን አሸናፊ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነበር የሚሉ ተንታኞች፥ ፑቲን ተቃዋሚዎችን በማሰር በምርጫው እንዳይሳተፉ አድርገዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።
የፑቲን ዋነኛ ተቀናቃኝ አሌክሲ ናቫልኒይ ከምርጫው በፊት በአርክቲክ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ ህይወቱ ማለፉም የአመቱ መነጋገሪያ ርዕስ እንደነበር ይታወሳል።
ትራምፕ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ
በህዳር ወር በአሜሪካ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም በድራማዊ ክስተቶች የተሞላ ነበር።
በሪፐብሊካኑ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የቀረቡ ከወሲባዊ ቅሌትና ማጭበርበር ጋር የተያያዙ በርካታ ክሶች፤ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ፤ የባይደን ከምርጫ ፉክክሩ መውጣት እና የካማላ ሃሪስ እና ትራምፕ ክርክር የአለምን ትኩረት ስበው ሰንብተዋል።
በተጠባቂው ምርጫ ትራምፕ 312 ወኪል መራጮች እና 77.3 ሚሊየን መራጮችን በማግኘት በከፍተኛ ብልጫ ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት አግኝተዋል።
አወዛጋቢው ሰው ሶስተኛ አመቱን የያዘውን የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት እና ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች ያለቁበትን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። ትራምፕ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ስደተኞችን አባርራለሁ ማለታቸውም ስጋት ፈጥሯል።
የኤኤንሲ ከ30 አመት በኋላ ዝቅተኛ ውጤት - የካጋሜ 29 አመት ስልጣን
ደቡብ አፍሪካ እና ሩዋንዳ በሀምሌ ወር ምርጫ አካሂደዋል።
በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ ለ30 አመታት በስልጣን ላይ የቆየው የኔልሰን ማንዴላ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ (ኤኤንሲ) በታሪኩ ለመጀመርያ ግዜ ዝቅተኛውን ድምጽ አግኝቷል። የሲሪል ራማፎሳ ፓርቲ በምርጫው 40 በመቶ ድምጽ በማግኘት ጥምር መንግስት ለመመስረት ተገዷል።
ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ባካሄደችው ሩዋንዳ ደግሞ ፖል ካጋሜ 99 ነጥብ 15 በመቶው ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው ይታወሳል። ሩዋንዳን ከፈረንጆቹ 2000 ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት እየመሩ የሚገኙት ካጋሜ ለ29 አመታት በስልጣን የሚያቆያቸውን ድምጽ አግኝተዋል።
ቱኒዚያ፣ ቻድ፣ ሴኔጋል እና ራስ ገዟ ሶማሌላንድ ምርጫ ያካሄዱትም በዚሁ የፈረንጆቹ አመት 2024 ነው።
የእስራኤል እና ኢራን ፍጥጫ ፤ የሃማስ እና ሄዝቦላህ መሪዎች ግድያ
2024 የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ጫፍ ላይ የደረሰበት አመት ነበር።
እስራኤል በጋዛ በጀመረችው ጦርነት ምክንያት በኢራን ይደገፋሉ በሚባሉ የፍልስጤሙ ሃማስ፣ የመኑ ሃውቲ እና በሊባኖሱ ሄዝቦላህ የሚሳኤልና ድሮን ጥቃት በብዛት ተፈጽሞባታል።
የሃማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ በሀምሌ ወር መጨረሻ በቴህራን መገደልም የእስራኤልና ኢራንን ውጥረት ከፍ አድርጎት ቴህራን ወደ ቴል አቪቭ ከ200 በላይ ሚሳኤሎችን ተኩሳለች። እስራኤልም በጥቅምት ወር በአጻፋው የኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ከፍታ ውጥረቱ ከፍ ብሎ ነበር።
ሃኒየህን የተኩት ያህያ ሲንዋር በጋዛ እና የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ በቤሩት በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውና የእስራኤል እግረኛ ጦር ወደ ሊባኖስ መግባትም የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረትን አባብሶት ነበር።
እስራኤል በርካታ የሄዝቦላህን መሪዎች ገድላ፤ በመሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ካደረሰች፤ ከ3 ሺህ 800 በላይ ሊባኖሳውያን ህይወት ካለፈ በኋላም ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ መጠነኛ መረጋጋት ተፈጥሯል።
የየመኑ ሃውቲ ግን እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን "ጭፍጨፋ" ካላቆመች የሚሳኤል ጥቃቱን እንደሚቀጥል በመዛት በየእለቱ ጥቃት እያደረሰ ነው፤ እስራኤልም በሰንአ እና ሆዴይዳህ በቡድኑ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት በማድረስ ላይ ናት። ሃውቲዎች ከኢራን የጦር መሳሪያ እንዳያገኙ በሚል የምትወስደው እርምጃም ከፍተኛ ውድመት አድርሷል።
እስራኤል በጋዛ፣ የመን፣ ሊባኖስ፣ ሶሪያ እና ኢራቅ "የኢራን ተላላኪዎች" በምትላቸው ሃይሎች እየወሰደችው ያለው እርምጃ የቀጠናውን ትኩሳት ሲያባብሰው ቢቆይም ቴል አቪቭ ትልቅ ድል አግኝቼበታለሁ ባለለች።
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በጥር 2024 የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ ከሞቃዲሾ ጋር የተካረረ አለመግባባት ውስጥ ገብታለች።
ስምምነቱ ሉአላዊነቴንና አለምአቀፍ ህግን ጥሷል ያለችው ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ማባረርን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዳለች። ከኤርትራ እና ግብጽ ጋር የሶስትዮሽ የትብብር ስምምነት የተፈራረመችውም በዚሁ የፈረንጆቹ አመት ነው።
አዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ ቅራኔ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ግብጽ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ አድርጋለች፤ በአዲሱ የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ውስጥ ወታደር እንደምታዋጣም ገልጻለች።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ልዑክ (አትሚስ)ን በሚተካው ተልዕኮ ውስጥ የመሳተፏ ጉዳይ እስካሁን አልታወቀም።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከወራት መካሰስ በኋላ በቅርቡ በቱርክ አደራዳሪነት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ለአንድ አመት የዘለቀውን ውጥረት እንደሚያረግብ ታምኖበታል።
ሶሪያ - የአሳድ የ53 አመት አገዛዝ መገርሰስ
ለ13 አመታት በእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገባችው ሶሪያ በ2024 ተስፋ ሰንቃለች።
አባታቸውን ተክተው ሶሪያን ለ24 አመታት የመሩት በሽር አል አሳድ ወደ ሩሲያ ኮብልለው ለለውጥ ስንታገል ነበሩ ያሉ አማጺያን በቅርቡ ደማስቆን ተቆጣጥረዋል።
ፈጣኑን አሳድን ከስልጣን የማንሳት ግስጋሴ የመራው የ"ሃያት ታህሪር አል ሻም" ቡድን አለቃው አህመድ አል ሻራ በጊዜያዊነት ስልጣን ይዘው የወደመችውን ሶሪያ መልሶ ለመገንባትና ህገመንግስት አሻሽሎ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ ናቸው።
አል ሻራ ሶሪያ የሁሉን ጎሳና ሃይማኖት በእኩል የሚታይባት ትሆናለች ብለው ቃል ቢገቡም የተከፋፈለችውን ሀገር ማጽናት ፈተና እንደሚሆንባቸው ይገመታል።
እስራኤል የሶሪያ ስትራቴጂካዊ የጦር መሳሪያዎች "በአክራሪዎች እጅ እንዳይገቡ" በሚል በተለያዩ የሶሪያ ከተሞች የምትፈጽመው ድብደባ መጠናከርና ጦሯን ድንበር አሳልፋ ማስገባቷ ሌላ ጦርነት እንዳይጠራ ተሰግቷል።
የሩሲያ፣ ኢራን፣ ቱርክ፣ አሜሪካ፣ እስራኤልና ሌሎች ሀገራት በሶሪያ ያላቸው የተለያየ ፍላጎትም በ13 አመቱ ጦርነት የወደመችውን ሶሪያ አበሳ ሊያስቀጥሉ ይችላሉ ተብሏል።
በ2024 የአለማችን የቀጣይ አምስት እና ከዚያ በላይ አመታት መጻኢ ይወስናሉ የተባሉ ምርጫዎች ተካሂደዋል። እነዚህ ምርጫዎች ለሚሊየኖች ሞት፣ መፈናቀልና ረሃብ መንስኤ የሆኑ ጦርነቶች እንዲቆሙ መፍትሄ የሚያስቀምጡ መሪዎችን ወደ ፊት አምጥተዋል? አለማችን የተደቀኑባትን ፈተናዎችስ ይፈቱታል የሚለው በቀጣይ የሚታይ ይሆናል።