ኢኮኖሚ
በ2024 ሀብታቸው በብዙ የተመነደገላቸው 10 ቢሊየነሮች
የአለማችን ቢሊየነሮች ሊጠናቀቅ በተቃረበው 2024 አመት 700 ቢሊየን ዶላር ሀብት አካብተዋል
የቴስላ ስራ አስፈጻሚው ኤለን መስክ ከ188 ቢሊየን ዶላር በማግኘት ቀዳሚው ነው
ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት እድሜ የቀረው 2024 በመላው አለም ለሚገኙ ቢሊየነሮች በሀብት ላይ ሀብት የጨመሩበት አመት ነው።
የፎርብስ መረጃ እንደሚያሳየው የቢሊየነሮች ቁጥር ወደ 2 ሺህ 781 ከፍ ብሎ አጠቃላይ ሀብታቸውም ከ14 ትሪሊየን ዶላር በላይ ደርሷል።
ቢሊየነሮች እስከ ታህሳስ 13 2024 ድረስ የጨመሩት ሀብት መጠንም 700 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ነው ፎርብስ የገለጸው።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ማበብ ብሎም የዶናልድ ትራምፕ ዳግም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኖ መምረጥ እንደ ኤለን መስክ ያሉ ቢሊየነሮች ሀብታቸው በብዙ እንዲመነደግ አድርጓል።
የቴስላ እና ስፔስኤክስ ስራ አስፈጻሚው ኤለን መስክ በ2024 ከ188 ቢሊየን ዶላር በላይ በማስገባት የአለማችን ቁጥር 1 ባለሃብትነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርም በፈረንጆቹ አመት ከፍተኛ ሀብት ያካበተ ሁለተኛው ሰው ሆኗል። የሜታ ስራ አስፈጻሚው በ2024 ከ91 ቢሊየን ዶላር በላይ በማግኘት አጠቃላይ ሀብቱን 214.4 ቢሊየን ዶላር አድርሷል።
በ2024 ከፍተኛ ሀብት ካካበቱ ቢሊየነሮች ሰባቱ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሪዎች ናቸው።