በ2024 የአለም ህዝብ ቁጥር በ71 ሚሊየን ጨመረ
የአለም ህዝብ ቁጥር በነገው እለት 8.09 ቢሊየን እንደሚደርስም የአሜሪካ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ ገልጿል
ህንድ በ2024ም የአለማችን ባለብዙ ህዝብ ሀገርነቷን አስጠብቃ ቀጥላለች
በ2024 የአለም ህዝብ ቁጥር በ71 ሚሊየን መጨመሩ ተነገረ።
በነገው እለት የፈረንጆቹ አዲስ አመት 2025 ሲገባም የአለም ህዝብ ቁጥር 8.09 ቢሊየን እንደሚደርስ የአሜሪካ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል።
በተገባደደው 2024 የአለም ህዝብ ቁጥር በ0.9 በመቶ አድጓል፤ ይሁን እንጂ ከ2023 የህዝብ ቁጥር እድገት (75 ሚሊየን) አንጻር ዝቅ ያለ ነው ተብሏል።
በጥር 2025 በየሰከንዱ 4.2 በመቶ ውልደት እና 2.0 ሞት እንደሚመዘገብ ተተንብዩዋል።
አሜሪካ በ2024 የነዋሪዎቿ ቁጥር በ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ጨምሮ በ2025 መግቢያ እለት አጠቃላይ የህዝብ ብዛቷ 341 ሚሊየን ይደርሳል ብሏል ቢሮው።
በጥር ወር 2025 በአሜሪካ በየዘጠኝ ሰከንዱ አንድ ህጻን ይወለዳል፤ በየ9.5 ሰከንዱ አንድ ሰው ይሞታል።
በየ23.2 ሰከንዱ ወደ አሜሪካ 1 ስደተኛ ይገባል ያለው የሀገሪቱ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ የውልደት፣ ሞትና ስደተኛ ምጣኔው ድምር በየ21.2 ሰከንዱ የሀገሪቱን ህዝብ ቁጥር በ1 እንደሚጨምር እንደሚያደርግ ጠቅሷል።
ወርልዶ ሜትር ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ህንድ በ2024 በህዝብ ቁጥሯ ላይ 13 ሚሊየን ጨምራ ቀዳሚነቷን አስቀጥላለች። የሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር በ2025 1.46 ቢሊየን እንደሚደርስም ተንብዩዋል።
የቻይና ህዝብ ቁጥር በ2024 ካለፈው አመት በ0.23 በመቶ (ከ3 ሚሊየን በላይ) ቀንሶ 1.419 ቢሊየን መሆኑንም መረጃው ጠቁሟል።
በነገው እለት 341,145,670 ህዝብ የሚኖራት አሜሪካ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የአሜሪካ ህዝብ ቁጥር በ2020ዎቹ በ2.9 በመቶ አድጎ የ9.7 ሚሊየን ጭማሪ አሳይቷል። እድገቱ በ2010ሮቹ ከነበረው የ7.4 በመቶ ግን ዝቅ ያለ ነው ተብሏል።