የአል ናስር አጥቂ ከሽልማቱ በኋላ ስለቀድሞ ክለቡ ዩናይትድ፣ ቪኒሺየስ ጁኒየር እና ፔፕ ጋርዲዮላ አስተያየቱን ሰጥቷል
ፖርቹጋላዊው የእግርኳስ ኮከብ በዱባይ በተካሄደው የ2024 የ"ግሎብ ሶከር አዋርድ" ሁለት ሽልማቶች ተበርክቶለታል።
የአል ናስሩ አጥቂ በመካከለኛው ምስራቅ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች እና የአለማችን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተብሎ ነው ሁለት ሽልማቶችን የወሰደው።
ከሽልማቱ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረገው ሮናልዶ የ2024/25 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በፈታኝ ወቅት ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ እንደሚያነሳ ግምቱን ተናግሯል።
የአውሮፓ ትልቁን ዋንጫ አምስት ጊዜ ያነሳው የእግርኳስ ፈርጥ "ማንቸስተር ሲቲ አሁን መጥፎ ጊዜው ቢሆንም ዳግም አንሰራርቶ ይመለሳል" ሲል ተደምጧል።
ስፔናዊው ፔፕ ጋርዲዮላ ድንቅ ብቃት ያለው አሰልጣኝ መሆኑን በመጥቀስም የክለቡ ተጫዋቾች ችግሮችን ነቅሰው በመለየት ወደተለመደው ድል እንዲመለሱ መነሳሳት ያስፈልጋቸዋል ብሏል።
ማንቸስተር ሲቲ በሻምፒዮንስ ሊጉ በስምንት ነጥብ 22ና ደረጃ ላይ መቀመጡና ጋርዲዮላም ጭምር በዚህ አመት ሻምፒዮንስ ሊጉን ላናነሳ እንችላለን ማለቱ ይታወሳል።
ሮናልዶ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከስድስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥብ ብቻ ሰብስቦ 20ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የቀድሞ ክለቡ ሪያል ማድሪድም ወደፉክክሩ መመለሱ እንደማይቀር በሙሉ ልብ ተናግሯል።
የሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቴንም "ከተጫዋቾች ጋር አንድ በአንድ እንዴት መደራደር እንዳለበት ጠንቅቆ የሚያውቅ ልዩ ሰው ነው" ሲል አሞካሽቶታል።
የ39 አመቱ ተጫዋች በቀድሞ ክለቡ ማንቸስተር ዩናይትድ ዙሪያም ሀሳቡን አጋርቷል። የሀገሩ ልጅ ሮበን አሞሪም ለኦልድትራፎርድ የቆዩ ችግሮች ተጠያቂ ሊሆን አይገባም ያለው ሮናልዶ ዩናይትድን ወደቀደመ ገናናነቱ ለመመለስ አሰልጣኝ መቀያየር ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ መናገሩን ጎል ስፖርት አስነብቧል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በቃለመጠይቁ ሌላው ያነሳው ጉዳይ የሪያል ማድሪዱ አጥቂን ቪኒሺየስ ጁኒየርን በተመለከተ ነው።
የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሮናልዶ "ሮድሪ ምርጥ ተጫዋች ቢሆንም ሻምፒዮንስ ሊግ ያነሳውና በፍጻሜው ድንቅ የነበረው ቪኒሺየስ ጁኒየር ማሸነፍ ነበረበት፤ ምርጫው ኢፍትሃዊ እንደነበር በአደባባይ ተናግሬያለሁ" ብሏል።
ቪኒሺየሽ የተሸለመው የፊፋ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት ከባሎንዶር የተሻለ መሆኑንም ገልጿል።