ስዊድን በአለማችን የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ መንገድ እየገነባች ነው
መንገዱ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በመነዳት ላይ እያሉ ሃይል የሚሞላ ነው ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት እስከ ፈረንጆቹ 2035 አዳዲስ ተሽከርካሪዎች በካይ ጋዝ የሚለቁ መሆን የለባቸውም የሚል ህግ አውጥቷል
ስዊድን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሸከርካሪዎች በመነዳት ላይ እያሉ ሃይል የሚሞላ መንገድ እየገነባች ነው።
የአለማችን የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ አውራመንገድ ከባድም ሆነ ቀላል ተሽከርካሪዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ለመሙላት መቆም ሳይጠበቅባቸው እየተጓዙ ሃይል ይሞላላቸዋል ተብሏል።
በሙከራ ደረጃ እየተገነባ ያለው መንገድ ሃልስበርግ እና ኦሬብሮ የተሰኙ ከተሞችን የሚያገናኝና 20 ኪሎሜትሮችን የሚሸፍን ነው።
ተሽከርካሪዎች ከኢ-መንገዱ(ኤሌክትሪክ መንገድ) ሃይል የሚሰበስቡበትን ሶስት አይነት አማራጮች እያጤነች መሆኑንና በቀጣይ እንደሚወሰንም ነው ስዊድን ያስታወቀችው።
500 ሺህ ኪሎሜትር የሚረዝሙ መንገዶች ያሏት ስዊድን በ2025 ወደ ስራ አስገባዋለው ያለችውን የኤሌክትሪክ መንገድ ፕሮጀክት ለማስፋት አቅዳለች።
ከጀርመን እና ፈረንሳይ ጋር በመተባበርም 3 ሺህ ኪሎሜትር የሚረዝም መጓዣ ብቻ ሳይሆን ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሃይል የሚሞላ መንገድ ለመገንባት ስለማሰቧም አስታውቃለች።
የኤሌክትሪክ መንገዱ ግንባታ ስዊድን የትራንስፖርት ዘርፉን ከካርበን ብክለት የጸዳ ለማድረግ የያዘችው እቅድ አካል መሆኑን የሀገሪቱ የትራንስፖርት እና ስትራቴጂክ ዴቨሎፕመንት ቢሮ ዳይሬክተር ጃን ፒተርሰን ተናግረዋል።
የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ወር አዲስ ተሽከርካሪዎች ምንም አይነት በካይ ካርበን የሚለቁ መሆን እንደሌለባቸው ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
ከ2035 ጀምሮ ለገበያ የሚቀርቡ ተሽከርካሪዎች የሃይል ምንጫቸው ከኤሌክትሪክ ወይም ከጸሃይ የሚመነጭ እንዲሆን ነው የህብረቱ አባል ሀገራት የተስማሙት።
በአለማችን የመጀመሪያውን የካርበን ታክስ በፈረንጆቹ 1991 ያስተዋወቀችው ስዊድን ከ2006 ጀምሮ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲመረቱ ድጋማ እያደረገች ነው።
50 ከመቶ ኤሌክትሪክ ከታዳሽ የሃይል ምንጮች የምታገኘው ሀገር፥ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እምርታን እያስመዘገበች መሆኑንም የዴይሊ ሜል ዘገባ ያሳያል።