የቱርክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ከአራት ዓመት በፊት በፕሬዝዳንትነት ኤርዶሀን ትዕዛዝ የተቋቋመ ነው
ቱርክ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ በሀገር ውስጥ አቅም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መስራቷን አስታውቃለች።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ኤርዶሀን ከአራት ዓመት በፊት ቱርክን ከውጭ ሀገራት ተገዝተው በሚገቡ ተሽከርካሪዎች ጥገኝነት ማላቀቅ የሚያስችል ኩባንያ እንዲመሰርት ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።
ቶግ በሚል ምህጻረ ቃል የተቋቋመው ይህ የአውቶሞቢል ኩባንያ ከአራት ዓመት በኋላ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምርቷል።
በዓመት 175 ሺህ ተሽከርካሪዎችን የማምረት አቅም ያለው ይህ ኩባንያ የመጀመሪያውን ተሽከርካሪ ቱርክ በተመሰረተችበት 99ኛ ዓመት ዕለት ለህዝብ ይፋ አድርጓል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
አሁን ላይ ኩባንያው አንድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን በ50 ሺህ ዩሮ ዋጋ ለገዢዎች ያቀረበ ሲሆን ቱርካዊያን ዋጋው ተወዷል በማለት ላይ ናቸው።
ኩባንያው በበኩሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በሀገር ውስጥ ላምርት እንጂ ከውጪ ሀገራት የሚገቡ ጥሬ እቃዎች ስላሉ ዋጋውን የግድ መጨመር አለብኝ ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በቀጣይ ግን ጥሬ እቃዎችን ከሀገር ውስጥ ሳገኝ የተሽከርካሪውን ዋጋ እንደሚቀንስም አስታውቋል።
በኩባንያው ምስረታ እና ምርት ምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን መገኘታቸውን ተከትሎ የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያው ከፖለቲካ እንዲርቅ ዜጎች በመጠየቅ ላይ ናቸው።
እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ማድረግ የሚያስችሉ መሰረተ ልምቶችም እንዲስፋፉላቸው ዜጎች ጠይቀዋል።
በቱርክ አንድ በነዳጅ የሚሰራ አዲስ ተሽከርካሪ በአማካኝ 500 ሊሬ ዋጋ ያለው ሲሆን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ለአብዛኛው የሀገሪቱ ዜጎች ውድ የሚባል እንደሆነም ተጠቅሷል።