በኤሌክትሪክ የሚሰራ አውሮፕላን የመጀመሪያውን በረራ አደረገ
የእስራኤሉ ኢቪዬሽን ኩባንያ በኤሌክትሪክ የሚሰራ አውሮፕላኑን ለስምንት ደቂቃ በአየር ላይ አብሯል
ሙከራው በአውሮፕላን ቴክኖሎጂ ታሪክ ከ50 ዓመት በኋላ የመጀመሪያው እንደሆነ ተገልጿል
በኤሌክትሪክ የሚሰራ አውሮፕላን የመጀመሪያውን በረራ አድርጓል።
የእስራኤሉ ኢቪዬሽን ኤርክራፍት የተሰኘው ኩባንያ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰራ አውሮፕላን የመጀመሪያውን በረራ አድርጓል።
ኩባንያው ከአሜሪካው ዋሸንግተን ኤርፖርት በመነሳት በ3 ሺህ 500 ጫማ ከፍታ ሁለት አብራሪዎች እና ሰባት ተሳፋሪዎችን በመያዝ የሙከራ በረራውን እንዳካሄደ ሲኤንኤን ዘግቧል።
የኩባንያው ስራ አስኪያጅ ግሪጎሪ ዳቪስ እንዳሉት በአውሮፕላን የሞተር ሀይል ታሪክ ከ1950ዎቹ በኋላ ሲለወጥ እንዳላዩ ተናግረዋል።
ላለፉት 70 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ሁሉም አውሮፕላኖች በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ነበሩ የሚሉት ስራ አስኪያጁ የአሁኑ ሙከራ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰራ አውሮፕላን ለማምረት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሆኑም አክለዋል።
የዚህን አውሮፕላን የባትሪ ቴክኖሎጂ ልክ በኤሌክትሪክ ቻርጅ ከሚሰሩት ተሽከርካሪዎች ጋር ተመሳሳይ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል።
የአንድ አውሮፕላን ቻርጅ የማድረጊያ ጊዜን በ30 ደቂቃ ውስጥ ለማድረግ ታቅዷል የተባለ ሲሆን የአውሮፕላኑን አሁናዊ ፍጥነት በሰዓት 287 ማይል ርቀት ይጓዛልም ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2015 ላይ የተቋቋመው ኢቪዬሽን ኩባንያ ከአራት ዓመት በኋላ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አውሮፕላኖችን ለዓለም ገበያ የማቅረብ እቅድ አስቀምጦ ነበር።
ይሁንና የኮሮና ቫይረስ እና ሌሎች የዓለም ክስተቶች ቡተቀመጠው ጊዜ የኤሌክትሪክ አውሮፕላኖችን አምርቶ ወደ ዓለም ገበያ ማድረስ እንዳልተቻለ ተገልጿል።
የአሜሪካ የአቪዬሽን ቁጥጥር ባለስልጣን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አውሮፕላኖቹን የጥራት ደረጃ እንዲገመግም እና እንዲመረቱ ፈቃድ እንዲሰጥ የማድረግ ስራው በቅርቡ እንደሚጀምርም ተቋም አስታውቋል።
ይህ አውሮፕላን የሙከራ በረራውን በስኬት አጠናቋል የተባለ ሲሆን በረራውን ጨርሶ ወደ ምድር ለማረፍ ግን የተወሰኑ ችግሮች አጋጥመዋል ተብሏል።
ከአንድ ዓመት በፊት የሙከራ በረራውን የማጠናቀቅ እቅድ የነበረው ይህ የአቪዬሽን ተቋም በመጥፎ የአየር ንብረት እና ኮሮና ቫይረስ ምክንያቶች ስራውን ባሰበው ጊዜ መከወን እንዳልቻለ ጠቁሟል።
በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ የሙከራ ጊዜውን በማጠናቀቅ በአሜሪካ ባሉ ግዛቶች መካከል የአገልግሎት መስጠት ሙከራዎችን እንደሚያከናውንም አስታውቋል።
በእቃ ማጓጓዝ ስራ ዘርፍ የተሰማሩ ንግድ ድርጅቶች ከወዲሁ የኤሌክትሪክ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል የተባለ ሲሆን ዲኤችኤል፣ ግሎባልኤክስ እና ሌሎችም ተቋማት ፍላጎት ካሳዩ ድርጅቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል።