ፎክስ ኒውስን ጨምሮ ከ100 በላይ ሚዲያዎች ባለቤት የሆኑት ሙርዶክ ከ20 ቢሊየን ዶላር በላይ ሃብት እንዳላቸው ይነገራል
የበርካታ መገናኛ ብዙሃን ባለቤቱ ሩፐርት ሙርዶክ ለአምስተኛ ጊዜ መሞሸራቸው ተሰማ።
የ93 አመቱ ቢሊየነር ከትናንት በስቲያ በካሊፎርኒያ ለ67 አመቷ ኤሌና ዙኮቫ ቀለበት አስረዋል።
ሙርዶክ አምስተኛ ባለቤታቸውን የተዋወቁት የቀድሞዋ ባለቤታቸው ቻይናዊቷ ዌንዲ ዴንግ አዘጋጅታው በነበረ ድግስ ላይ ነበር ተብሏል።
ባለፈው አመት ከአራተኛ ሚስታቸው አና ሌስሊ ስሚዝ ጋር ፍቺ የፈጸሙት ትውልደ አውስትራሊያዊ ቢሊየነር የስድስት ልጆች አባት ናቸው።
አውስትራሊያዊቷን የበረራ አስተናጋጅ ፓትሪሺያ ቦከር በማግባት አሃዱ ያሉት ሩፐርት ሙርዶክ፥ ስኮትላንዳዊቷን ጋዜጠኛ አና ማን እና አሜሪካዊቷን ሞዴልና ተዋናይ ጄሪ ሃል አግብተው ነበር።
አምስተኛ ሚስታቸው ኤሌና ዙኮቫም የሩሲያዊው ቢሊየነር አሌክሳንደር ቦከር የቀድሞ ባለቤት ነበሩ ተብሏል። ኤሌና ከአሌክሳንደር የወለደቻት ዳሻ የተባለች ልጃቸውም የቀድሞው የቼልሲ ባለሃብት ሮማን አብራሞቪች ሚስት እንደነበረች ነው ቢቢሲ የዘገበው።
በ93 አመታቸው ለአምስተኛ ጊዜ የተሞሸሩት ሩፐርት ሙርዶክ ፎክስ ኒውስ፣ ወል ስትሪት ጆርናል፣ ዘ ሰን፣ ዘ ታይምስን ጨምሮ ከ100 በላይ ሚዲያዎችን በስሩ የያዘው ኒውስ ኮርፖሬሽን ባለቤት ናቸው።
ሙርዶክ በ1950ዎቹ በአውስትራሊያ የጀመሩትን የሚዲያ ቢዝነስ ከ20 ቢሊየን ዶላር በላይ ሃብት እንዲያካብቱ አድርጓቸዋል።
በ1969 የእንግሊዞቹን ጋዜጦች ኒውስ ኦፍ ዘ ወርልድ እና ዘ ሰን፤ በሂደትም የአሜሪካዎቹን ኒው ዮርክ ፖስት እና ወል ስትሪት ጆርናል የገት ሙርዶክ፥ በፈረንጆቹ 1996 በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ከፍተኛ ተመልካች ያለውን ፎክስ ኒውስ መግዛታቸው ይታወሳል።
በ2013 የተቋቋመው ኒውስ ኮርፖሬሽንም ከ100 በላይ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንን በባለቤትነት የሚያስተዳድር ሲሆን፥ ሙርዶክ እስከባለፈው አመት የኮርፖሬሽንኑ ሊቀመንበር ነበሩ።
የኒውስ ኮርፖሬሽንንም ሆን የፎክስ ኒውስ ስራ አስፈጻሚነቱን ለልጃቸው ላችላን ያስተላለፉት ሩፐርት ሙርዶክ ከአዲሷ ባለቤታቸው ኤሌና ዙኮቫ ጋር የጫጉላ ሽርሽር ላይ ናቸው።