አልደሪን በ1969 በታሪካዊው የአፖሎ 11 ጉዞ ከኒል አሮምስትሮንግ ጋር ወደ ጨረቃ መጓዛቸው ይታወሳል
የአሜሪካው የቀድሞ የጠፈር አብራሪ በዝ አልደሪን በ93 አመታቸው አራተኛውን ጋብቻቸውን ፈፅመዋል።
አልደሪን በታሪካዊው የአፖሎ 11 ከኒል አሮምስትሮንግ ጋር ጨረቃን ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጡ አሜሪካዊ ናቸው። ይህን ጉዟቸውንም ከ600 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቴሌቪዥን እንደተመለከቱት መረጃዎች ያወሳሉ።
ይህም በወቅቱ ከፍተኛውን ተመልካች በማግኘት በክብረወሰንነት ተመዝግቦ እንደነበርም የሚታወስ ነው።
የቀድሞው አብራሪ ከአኒካ ፋውር ጋር በፈፀሙት ጋብቻ መደሰታቸውንና የለጋ ወጣትነት ስሜት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
የ93 አመቱ አዛውንት ወደ ጨረቃ ከተጓዙና በህይወት ካሉ አራት ግለሰቦች አንዱ መሆናቸውን ኤቢሲ ኒውስ አስታውሷል።
አልደሪን "በ93ኛ አመት የልደት ቀኔ ለረጅም ጊዜ የፍቅር ጓደኛዬ አኒካ ፋወር ቀለበት ማድረጌን ማሳወቅ እወዳለሁ" የሚል ፅሁፍን በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
የ63 አመቷ አኒካ ፋወር በኬሚካል ኢንጂነሪንግ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን የአልደሪን ኩባንያ "በዝ አልደሪን ቬንቸርስ" ምክትል ፕሬዝዳንት መሆናቸው ተገልጿል።
ከአፖሎ 11 የጨረቃ ጉዞ በኋላ ዝናቸው የናኘው አልደሪን፥ ከመገናኛ ብዙሃን ተሰውረው ቆይተዋል።
በፈረንጆቹ 2001 ከሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋር ባደረጉት ቆይታም፥ ከታሪካዊው ጉዞ በኋላ "ከህዝብ እይታ የራቅኩት ስላላሰብኩበት ወይም ምቾት ስለማይሰጠኝ ይሆናል" ብለው ነበር።
ከአፖሎ 11 ተልዕኮ በፊት በኮሪያ ጦርነት የአሜሪካ አየር ሃይል ተዋጊ አውሮፕላኖችን ያበረሩት በዝ አልደሪን፥
በ93 አመታቸው አራተኛውን ጋብቻቸውን ፈፅመው ዳግም የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነዋል።