ኢንዶኔዥያ ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ ወሲብን በወንጀል የሚያስቀጣ ህግ ልታጸድቅ ነው
ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ ጾታዊ ግንኙነት አንድ አመት እንደሚያስቀጣም በረቂቅ ህግ ተመላክቷል
የህግ ማሻሻያው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትን መሳደብም ጭምር የሚከለክል ነው
የኢንዶኔዥያ ፓርላማ ከጋብቻ ውጪ ወሲብ መፈጸም እስከ አንድ አመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጣ አዲስ የወንጀል ህግ ሊያጸድቅ ነው ተብሏል፡፡
ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖርም ጭምር የሚያግድ ነው የተባለው አዲሱ ህግ በታህሳስ 15 ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም የኢንዶኔዥያ የፍትህ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር ኤድዋርድ ኦማር ሻሪፍ ሂሪዬይ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
"ከኢንዶኔዥያ እሴቶች ጋር የሚስማማ የወንጀል ህግ በማግኘታችን ኩራት ይሰማናል"ም ብለዋል ሚኒስተሩ።
በረቂቁ ውስጥ የተሳተፉት የህግ አውጭ የሆኑት ባምባንግ ዉሪያንቶ አዲሱ ህግ በቅርቡ እንደሚጸድቅ ተናግረው፤ ህጉ በኢንዶኔዥያ ዜጎች እና የውጭ ዜጎች ላይ ተፈጻሚ የሚሆን እንደመሆኑ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በሆነችው ሀገር ገጽታ ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ ሊፈጥር እንደሚችል ያላቸውን ስጋት አስቀምጠዋል፡፡
ረቂቁን ወግ አጥባቂነት እየተስፋፋባት ባለችው ሀገር የአንዳንድ እስላማዊ ቡድኖች ድጋፍ ቢያገኝም ፤ በርካቶች እንደፈረንጆቹ የአምባገነኑ መሪ ሱሃርቶ በ1998 ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ የወጡትን የሊበራል ማሻሻያዎችን የሚቀለብስ ነው በሚል ተቃውሞዋቸውን እየገለጹ ነው፡፡
አሁን በሀገሪቱ ፓርላማ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ረቂቅ በ2019 እንዲጸድቅ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቃውሞ ማስነሳቱን ተከትሎ በይደር አመታት መሻገሩ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለይ የሞራል እና የመናገር ነጻነትን ይገድባሉ ያሏቸውን ህጎችን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ነበር፡፡
ተቺዎች ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በህጉ ላይ አነስተኛ ለውጦች ተደርገዋል ይላሉ፡፡
የተደረጉት ማሻሻያዎች ከ10 አመት መልካም የስነ ምግባር ባህሪይ በኋላ የሞት ቅጣትን ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀየር የሚያስችል ድንጋጌም ጭምር የሚያካትቱ ናቸው፡፡
ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ ጾታዊ ግንኙነት አንድ አመት እንደሚያስቀጣም በረቂቅ ህጉ ተመላክቷል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም የህግ ማሻሻያው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትን ወይም የመንግስት ተቋማትን መሳደብ እና ከኢንዶኔዥያ መንግስት ርዕዮተ ዓለም ጋር የሚቃረኑ ሃሳቦችን መግለጽ ይከለክላል።
ፕሬዝዳንቱን መሳደብ፣ ሶስት አመታት ሊያሳስር እንደሚችልም በህጉ ተደንግጓል፡፡
በብዛት የሙስሊም ሀገር እንደሆነች የሚነገርላት ኢንዶኔዥያ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን እና ሃይማኖታዊ አናሳዎችን በእኩል የማያስተናግድና አግላይ ህግ ተግባራዊ እንደምታደርግ ይገለጻል፡፡