የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት የበኩር ልጃቸውን የሀገሪቱ ጦር አዛዥ አድርገው ሾሙ
አዲሱ ሹመት ሙሴቪኑ ልጃቸውን ለፕሬዚዳንትነት እያዘጋጁት ነው የሚል ጥርጣሬን አጭሯል
የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ አዲስ የካቢኔ ሹም ሽር አድርገዋል
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የበኩር ልጃቸው ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባን የሀገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ አድርገው መሾማቸው ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ከሰሞኑ አዲስ የካቢኔ ሹም ሽር ማድረጋቸውን ተከተሎ ነው ልጃቸውን የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ዋና አዛዥ አድርገው የሾሙት።
አዲሱን ሹመት ተከትሎም ፕሬዝዳንት ሙሴቪኑ ልጃቸው ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ የፕሬዚዳንትነት ስፍራን እንዲረከባቸው እያዘጋጁት ነው የሚል ጥርጣሬን አጭሯል።
ከዚህ ቀደም የኡጋንዳ መከላከያ ሰራዊት የምድር ጦር አዛዥ የነበሩት ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ በፈረንጆቹ 2022 ከኬንያ ጋር እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከሰጡት ያልተገባና ጠብ አጫሪ ንግግር ጋር በተያያዘ ካኃላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ ከፈረንጆቹ 2022 ወዲህ የፕሬዝዳንቱ የልዩ ዘመቻዎች ጉዳይ አማካሪ በመሆን በማገልገል ላይ ቆይተዋል።
ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ የኡጋንዳ ጦር ዋና አዛዥ ሆነው የተሸሙት ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ትናንት ሃሙስ ባደረጉት የካቢኔ ሹም ሽርን ተከትሎ ነው ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በአዲሱ የካቢኔ ሹም ሽራቸው አምስት ሚኒስትሮችን ከኃላፊነት ማንሳታቸውም ተነግሯል።
በዚህ መሰረት የኡጋንዳ ጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ጄነራል ዊልሰን ማብዲ የንግድ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውንመ ተሰምቷል።
በተጨማሪም የፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ልጅ የሆኑት የጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ የቅርብ አማካሪ የነበሩ ሁለት ሰዎች በሚኒስትርነተ መሾመቸው ነው የተገለጸው።
ከፈረንጆቹ 1986 አንስቶ ላፉት 38 ዓመታት ኡጋንዳን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ስልጣናቸውን ለልጃቸው ሙሆዚ ካይኔሩጋባ ለማስተላለፍ እያጤኑ ነው ቢባልም፤ ፕሬዝዳነቱ ግን ይህንን ያጣጥላሉ።
ላለፉት 20 ዓመታት በኡጋንዳ ወታደራዊ ተቋም ውስጥ ያለፈው ሙሆዚ ካይኔሩጋባ ከዚህ ቀደም ራሱን ለሀገሪቱ መሪነት ለማዘጋጀት በማሰብ ከሀገሪቱ ጦር ራሱን አግልሎ እንደነበረ አይዘነጋም።
የዮዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ በወቅቱ ራሱን ከሀገሪቱ ጦር ያገለለው እ.ኤ.አ በ2026 የሀገሪቱ መሪ ለመሆን ዝግጅት ለማድረግ እንደሆነ ምልክቶች አሉ ተብሎ ነበር።
ኡጋንዳ በፈረንጆቹ 2026 ላይ አጠቃላይ ምርጫ እንደምታደርግ ይጠበቃል።