የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ኬንያዊያንን ይቅርታ ጠየቁ
ፕሬዝዳንቱ ይቅርታ የጠየቁት የበኩር ልጃቸው ጀነራል ምሁዚ ስለ ኬንያ በትዊተር ገጻቸው ያልተገባ ነገር በመጻፋቸው ነው
የኡጋንዳ ምድር ሀይል አዛዥ ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ ከኃላፊነት መነሳታቸው ይታወሳል
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ኬንያዊያንን ይቅርታ ጠየቁ።
የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የበኩር ልጅ የሆኑት ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ ትዊተር በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እሳቸው የሚመሩት የኡጋንዳ ምድር ጦር ኬንያን በሁለት ሳምንት ውስጥ ይቆጣጠራል ብለው ነበር።
የጀነራሉን የትዊተር መልዕክት ተከትሎም በርካቶች በጉዳዩ ዙሪያ ሃሳባቸውን በቀልድም በቁምነገርም የጻፉ ሲሆን ኬንያ ቅር መሰኘቷ ተገልጿል።
ይሄንን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ልጃቸው ያደረገው ድርጊት ትክክል ባለመሆኑ እና ኬንያዊያን በማስቆጣቱ ምክንያት ይቅርታ ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ በልጃቸው ያልተገባ የትዊተር መልዕክት ምክንያት ማዘናቸው የተገለጸ ሲሆን ካለበት የምድር ሀይል አዛዥነት ማንሳታቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
ኡጋንዳ ከኬንያ ጋር ማንኛውንም ጉዳይ በቀጥታ ወይም በምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ መድረክ እና በአፍሪካ ህብረት ስር መነጋገር እየተቻለ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ መጻፍ ችግር አይፈታም ሲሉም ፕሬዝዳንቱ በይቅርታ ደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል።
የኡጋንዳ ምድር ሀይል አዛዥ የነበሩት ሌተናል ጀነራል ኬንሩጋባ የሙሉ ጀነራልነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው የፕሬዝዳንቱ ልዩ ዘመቻዎች አማካሪ ሆነው መሾማቸውም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ በደብዳቤያቸው ላይ አክለውም የጀነራል ማዕረግ ለልጃቸው የሰጡት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ስለ ሌላ ሉዓላዊ ሀገር ያልተገባ ነገር ቢጽፍም በሌሎች የስራ ዘርፋቸው ደግሞ የሚያሸልማቸውን ስራ በመስራታቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።
ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ የ78 ዓመቱን የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒን እንደሚተካ በተደጋጋሚ ቢገለጽም ጀነራሉ ግን በማህበራዊ የትስስር ገጾች የሀገሪቱን ዲፕሎማሲ እና ፕሮቶኮል የሚያበላሹ መልዕክቶችን በማጋራት ላይ ናቸው።
ጀነራል ሙሁዚ ከኬንያ ባለፈ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስለ ሌሎች ሀገራትም የውስጥ ጉዳዮች በመጻፍ ይታወቃሉ።