የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮዎሪ ሙሴቬኒ ልጅ ከሀገሪቱ ጦር አዛዥ ስልጣን መልቀቁ ተሰማ
ሌፍተናንት ጄነራሉ ጡረታ ስለወጣበት ምክንያት በዝርዝር አልተናገረም ተብሏል
የፕሬዚዳንቱ ልጅ ስልጣን የለቀቀው የሀገሪቱ መሪ ለመሆን በማሰብ እንደሆነ ተገልጿል
የኡጋንዳ ጦር ኃይሎች አዛዥ የሆነው የፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ ከኃላፊነቱ ራሱን በጡረታ ማግለለን አስታውቋል።
ላለፉት 20 ዓመታት በኡጋንዳ ወታደራዊ ተቋም ውስጥ ያለፈው ሙሆዚ ካይኔሩጋባ አሁን ስልጣን የለቀቀው የሀገሪቱ መሪ ለመሆን በማሰብ እንደሆነ ተገልጿል። በዚህም መሰረት ሌፍተናንት ጄነራሉ ከዛሬ ጀምሮ ጡረታ መውጣቱን ይፋ አድርጓል።
የዮዎሪ ሙሴቬኒ ልጅና የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጡረታ የወጣው እ.ኤ.አ በ2026 የሀገሪቱ መሪ ለመሆን ዝግጅት ለማድረግ እንደሆነ ምልክቶች አሉ ተብሏል።
በርካታ ኡጋንዳውያን ካይኔሩጋባ አባቱን በመተካት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ ተብሏል።
የዮዎሪ ሙሴቬኒ ልጅ ባለፉት 28 ዓመታት በሀገሩ ጦር ውስጥ ሲሰራ እንደነበር ገልጾ ጦሩም “በዓለም ትልቁ” እንደሆነ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል። ጡረታ ለመውጣቱ ምንም አይነት ምክንያት አልሰጠምም ነው የተባለው።
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1986 ጀምሮ ኡጋንዳን እየመሩ ያሉት የ 77 ዓመቱ ዮዌሪ ሙሴቬኒ “ስልጣኑን ለልጃቸው ሊያስተላልፉ ይችላሉ” የሚለውን ጉዳይ በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።
ይሁንና የልጃቸው ካይኔሩጋባ ደጋፊዎች ሀገሪቱን ለመምራት ትክክለኛው ሰው እንደሆነ እየገለጹ ናቸው ተብሏል።
ሌፍተናንት ሙሆዚ ካይኔሩጋባ ሩሲያ በዩክሬን ያደረገችውን ወታደራዊ ተልዕኮ መደገፋቸው የሚታወስ ነው። ምንም እንኳን የኡጋንዳ ሕግ ወታደር በፖለቲካ እንዲሳተፍ ባይፈቅድም የ47 ዓመቱ የሙሴቬኒ ልጅ ግን የሀገሪቱ መሪ ሊሆን እንደሚችል እየተገመተ ነው።
ካይኔሩጋባ በይፋ የአባቱን ቦታ ስለመተካት ባይናገርም ደጋፊዎቹ ግን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ስለሱ ሲያወሩ ይሰማል ተብሏል።
የመብት ተሟጋቾች ዮዎሪ ሙሴቬኒ ተቃዋሚዎቻቸውን በማሰርና በማንገላታት ይከሷቸዋል።
ሙሴቬኒ ባሳለፍነው ጥር የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኙን ቦብ ዋይንን በማሸነፍ ስልጣኑን እንደያዙ ቢቆዩም ሙዚቀኛው ተፎካካሪያቸው ግን ውጤቱን ውድቅ አድርጎታል።